The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
የጆሀሪ መስኮቶች ከሰው ጋር እንዲሁም ከራሳችን ጋር ያለንን ግንኙነት በተሻለ ለመረደት የሚያግዝ ንድፍ ነው፡፡ ጆሀሪ ስያሜውን ያገኘው ንድፉን በጋራ ከፈጠሩት የስነ ልቦና ባለሞያዎቹ ጆሴፍ ለፍት እና ሀሪንግተን ኢንግሀምን ስም በማቀናጀት ነው፡፡ ማንነታችን በአራት ሊከፈል ይችላል፦ ግልፅ፣ ድብቅ፣ የተሰወረ እና ጨለማ፡፡
- ግልፁ ማንነት፦ ይሄኛው ስለራሳችን እኛም ሌላውም ሰው የሚያውቀው ሲሆን ድርጊቶችን፣ እውቀትን፣ ክህሎትን ያጠቃልላል፡፡ ስለዚህኛው ማንነታችን ከሰዎች ጋር ለመነጋገር ችግር የለብንም በተጨማሪም ሰዎች ስለዚህ የማንነታችን ክፍል በሚሰጡት አስተያየት በብዛት እንስማማለን፡፡
- ድብቁ ማንነት፦ ይህ ማንነት ራሳችን የምናውቀው ሲሆን ከሌሎች የተደበቀ ነው፡፡ በዚህ መስኮት ውስጥ ያሉ ማንነቶቻችንን ስለምናፍርባቸው ወይም የግል ህይወታችን ስለሆኑ ተጋላጭ እንዳንሆን ከሌሎች እንደብቃቸዋለን፡፡ በተመሳሳይ በትህትና ምክኒያት ሰዎች እንዲያውቁ የማንፈልጋቸው ችሎታዎቻችን እውቀታችንንም ያካትታል፡፡
- የተሰወረ ማንነት፦ ይሄኛው ሌሎች ሰዎች የሚያዩት ከኛ ግን የተሰወረው ማንነት ነው፡፡ ምክኒያታዊ እንደሆንን እናስብ ይሆናል ሰዎች ግን ግትር እንደሆንን ነው የሚያውቁት፡፡ ወይም ራሳችንን 'ምንም እንደማያውቅ 'ልናስብ እንችላለን ሰዎች ግን በጣም ብልህና አስተዋይ እንደሆንን ሊረዱ ይችላሉ፡፡ በዚህ መስኮት ውስጥ ነው ሰዎች ቃላችን እና ድርጊታችን እንደሚለያይ የሚያስተውሉት፡፡
- ጨለማ (የማይታወቀው) ማንነት፦ ይህ ማንነት በራሳችንም ሆነ በሌሎች የማይታወቅ ክፍል ነው፡፡ ጥሩም ጥሩ ያልሆኑ ሀሳቦች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡
በአጠቃላይ የ ጆሀሪ መስኮቶቸ ራሳችንን ለመረዳት ከዚያም ለማገጎልበት እንዲሁም ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚኖረንን ግንኙነት ለማሻሻል የሚያግዝ ንድፍ ነው፡፡
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment