The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
ይህ በጆን ካባት-ዚን የተፃፈው ምርጥ መፅሀፍ ርዕስ ነው፡፡ ርዕሱ እንደሚገልፀው የትም ቦታ ብንሄድ ራሳችንን ይዘን ነው፡፡ አስፈላጊነቱ "ሌላ ቦታ በሆንኩኝ!" እያሉ መመኘትን እንድናቆም ነው፡፡ እረፍት ላይ ብሆን፣ ከሌላ ፍቅረኛ /የትዳር አጋር ጋር ብሆን፣ ሌላ ትምህርት ተምሬ ቢሆን፣ ሌላ ስራ ቢኖረኝ፣ ሌላ ቤት ውስጥ ብኖር፣ ሌላ ሁኔታ ውስጥ ብሆን...ደስተኛ እሆን ነበር ብለን እናስባለን፡፡ ደስተኛ አንሆንም!
በእውነታው ጎጂ የሆነ የአስተሳሰብ ልማድ ካለን ማለትም በቀላሉ የምንናደድ ከሆነ፣ ትንንሽ ነገሮች የሚያበሳጩን ከሆነ፣ ነገሮች የተለዩ ቢሆኑ ብለን የምንመኝ ከሆነ የትም ብንሄድ እነዚህ ልማዶች ይከተሉናል፡፡ በተቃራኒውም ደግሞ እውነት ነው፡፡ በአብዛኛው በትንሹ የማይናደድ ደስተኛ ሰው ከሆንን ቦታ ብንለውጥም ከሌላ ሰው ጋር ብናሳልፍም ሳንጨነቅ ጥሩ ጊዜ ይኖረናል፡፡
አንድ ጊዜ አንድ ሰው "እናንተ አካባቢ ያሉ ሰዎች ምን አይነት ናቸው?" ብሎ ጠየቀኝ፡፡ እኔም መልሼ "መጀመሪያ እናንተ አካባቢ ያሉት ሰዎች ምን አይነት ናቸው?" ብዬ ጠየቅሁት፡፡ "ስግብግብና ራስ ወዳድ ናቸው፡፡" ብሎ መለሰልኝ፡፡ "እኛ አካባቢ ያሉትንም ሰዎች እንደዚያው የምታገኛቸው ይመስለኛል፡፡" አልኩት፡፡
ህይወት እንደመኪና ከውስጥ ወደ ውጭ እንደሚሽከረከር ስንገነዘብ አስገራሚ ነገሮች መፈጠር ይጀምራሉ፡፡ ከውጭ ወደ ውስጥ አይሆንም! ሌላ ቦታ፣ ሌላ ሁኔታ ቢሆን የሚለውን ምኞት ትተን አሁን ያለንበትን ቦታ የተሻለ ማድረግ ላይ ስናተኩር አሁን እዚሁ ደስተኛ መሆን እንጀምራለን፡፡ ከዛ ቦታ ብንለውጥም፣ አዲስ ነገር ብንሞክርም፣ አዲስ ሰዎች ስናገኝም ውስጣዊ እርጋታችንን ይዘን ነው፡፡ የትም ቦታ ብንሄድ ራሳችንን ይዘን ነው፡፡
ከዶ/ር ሪቻርድ ካርሰን 'ቀላሉን ነገር አታካብድ.....እናም ሁሉም ቀላል ነገር ነው፡፡' መፅሀፍ ገፅ 133-134 የተተረጎመ
በደስተኝነታችንን እና በኛ መካከል ጣልቃ ሊገባ የሚችለው ሌላኛው ብቸኛ ሰው መስታወት ውስጥ የምንመለከተው እኛኑ የሚመስለው ግራኝ ሰው ብቻ ነው፡፡
መልካም ጊዜ!
እውነት ነው እናመሰግናለን ተባረክ♥
ReplyDelete