The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
ልጆች የሚያድጉበት መንገድ ከፍ ሲሉ ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት፣ የፍቅር ጓደኛ ምርጫ፣ ስኬት፣ በራስ መተማመን ላይ ትልቅ ሚና አለው፡፡ በተጨማሪም ከሴክስ፣ከገንዘብና ከአማች ቀጥሎ ትዳር ውስጥ አለመግባባት የሚፈጥረው የልጆች አስተዳደግ ነው፡፡ እንደ የስነ-ነልቦና ባለሞያዎች ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያሳድጉባቸው መንገዶች በአራት ይከፈላሉ፡፡
- አምባገነን (ኮስታራ) ፦ ይህ አይነት የልጅ አስተዳደግ በአለማችን በይበልጥ ደግሞ በሀገራችን ለረጅም ጊዜ የነበረ የማሳደጊያ መንገድ ነው፡፡ ከእናቶች ይልቅ ደግሞ አባቶች ላይ ይስተዋላል፡፡ እነዚህ ወላጆች ልጆቻቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው 'ኮስተር' ብለው ይነግሩና ልጆች 'ወለም ዘለም' ሳይሉ እንዲከተሉ ይጠብቃሉ፡፡ እንደዚህ የሚያድጉ ልጆች በአብዛኛው ስኬታማ ለመሆንና 'ትክክል' የሆኑ ነገሮችን ለማድረግ የሚጣጣሩ ሲሆኑ አዲስ ነገር ለመሞከር ወይም ያልተለመደ ስራ ለመስራት ይከብዳቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ከቤተሰብ ሲርቁ የማያምኑባቸውን ነገሮች ለማድረግ ይገፋፋሉ፡፡
- የሚያሞላቅቁ (ሁሉንም የሚፈቀዱ)፦ ይሄ የልጅ አስተዳደግ በቅርብ የተጀመረ ሲሆን በከተማዎች በጣም እየተስፋፋ የመጣ አይነት ነው፡፡ እነዚህ ወላጆች ልጆቻቸው ያለ ገደብ እንደፈለጉ አንዲሆኑ ይፈቀዳሉ፡፡ ልጆቻቸው ያለ ከልካይና ያለ ገደብ እንደልባቸው እንዲሆኑ ከመፍቀድ ውጪ ምን ማድረግ እንዳለባቸው አይነግሯቸውም፡፡ ልጆቻቸው እስከፈለጉ ድረስ ከቤተሰቡ አቅም በላይ ቢሆንም እንኳ ለማሟላት ይጣጣራሉ፡፡እንደዚህ የሚያድጉ ልጆች ከቤት ውጭ እንደፈለጉ መሆን ስለማይችሉ ጭንቀት ይሰማቸዋል፡፡ የተወሰኑት ለምንም ነገር ሀላፊነት የማይሰማቸው ይሆናሉ፡፡
- ግድ የለሽ፦ እነዚህ ወላጆች ለልጆቻቸው ግድ የሌላቸው ሲሆኑ ቁጣም ሆነ አድናቆት አያሳዩም፡፡ ልጆቻቸው እነሱን እስካላስቸገሩ ድረስ የትም ቢውሉ፤ የፈለጉትን ቢያደርጉ ግድ አይሰጣቸውም፡፡ እንደዚህ የሚያድጉ የተወሰኑት የቤተሰብ ሀላፊነት ስለሚሸከሙ ልጅነታቸውን ይነጠቃሉ፡፡ ሲያድጉ ብቸኝነት የሚሰማውና ሰውን ማመን የሚከብደው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በራስ መተማመናቸው ዝቅተኛ( ወይም ለማካካስ በጣም ከፍተኛ) ሊሆን ይችላል፡፡
- በልክ (ነጻነት በወሰን የሚሰጡ) ፦ እነዚህ ወላጆች ለልጆቻቸው ወሰን አስቀምጠው ነጻ እንዲሆኑ የሚፈቅዱ ሲሆኑ የልጆቻቸውን ምርጫ ያከብራሉ፡፡ እነዚህ ወላጆች የልጆቻቸውን ሀሳብ፣ ስሜትና አስተያየት ያዳምጣሉ፡፡ በጣም ጠቃሚ ነገሮች ላይ የሚወስኑት ወላጆች ናቸው፡፡ በአቅማቸው የሚችሉትን ያደርጋሉ፡፡ በዚህ መንገድ የሚያድጉ ልጆቸ ከሌሎች ጋር ተባብረው መስራት የሚችሉና በራሳቸው የሚተማመኑ ስኬታማ ሰዎች ይሆናሉ፡፡
የአንድን ሰው የወደፊት ባህሪ የሚወስኑ ከአስተዳደግ ባሻገር በጣም ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከላይ የተገለፀው አስተዳደግ ሊኖረው የሚችለውን ተፅእኖ በደፈናው ለማሳየት የቀረበ ነው፡፡
የነገውን ፍሬ ዛሬ አበባው ላይ የምናደርገው እንክብካቤ ይወስነዋል፡፡ ስለ ሴክስ፣ ስለ ገንዘብና ስለ አማች በሌላ ጊዜ ይቀርባል፡፡
Comments
Post a Comment