The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
የአእምሮ ህክምና ውጤቱ በአጠቃላይ ጥሩ ነው፡፡ ከሌሎች የህክምና ስፔሻሊቲዎች (የውስጥ ደዌ፣ የቀዶ ህክምና፣ የህፃናት ህክምና...ወዘተ) ጋር ተነፃፃሪ የሆነ ውጤት ያመጣል፡፡ ሁሉም የህክምና ስፔሻሊቲዎች እንደሚታከሙ ሰዎች የተወሰኑ ሰዎች ለውጥ ላያሳዩ እንዲሁም እጅግ በጣም ጥቂቶች ላይ ህመሙ ሊባባስ ይችላል፡፡ ከአእምሮ ህክምና ጥሩ ውጤቶች ይልቅ " የአማኑኤል መድሃኒት ከወሰደ በኋላ ህመሙ ባሰበት፡፡" ፣ "የአማኑኤል መድሀኒት ያጀዝባል፡፡" እና የመሣሠሉት አባባሎች ጎልተው ይሰማሉ፡፡ ለምን? ምክኒያቶቹን ከፋፍሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡
1. የህመሙ አይነት፡-
አብዛኛዎቹ የአእምሮ ህመሞች ( ዘጠና አምስት ከመቶ በላይ)ለአጭር ጊዜ የሚቆዩ ወይም በቀላሉ ሊታከሙ የሚችሉ ሲሆኑ በጣም ጥቂቶቹ የረዥም ጊዜ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ ምልክቱ ሳል ቢሆን በአብዛኛው ጉንፋን ሊሆን እንደሚችል እና በጣም በጥቂቶች ቲቢ እንደሚሆነው ማለት ነው፡፡በአብዛኛው ታካሚዎች አማኑኤል ሆስፒታል የሚሄዱት ብዙ ነገሮች ከተሞከሩ በኋላ እንደመጨረሻ አማራጭ ነው፡፡ አንድ ሰው ሳይታከም ረጅም ጊዜ ከቆየ ከህክምና የሚገኘው ውጤት እንደሚጠበቀው አይሆንም፡፡
2.የህክምና ሁኔታ፦
አማኑኤል ሆስፒታል በሀገራችን ብቸኛው የአእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እንደመሆኑ ከፍተኛ የሆነ መጨናነቅ ይስተዋላል፡፡ በስራ ጫና ፣በሀኪሞች መቀያየር የህመሙን አይነትና መጠን አለመለየት፣ መድሃኒቶችን ከሚያስፈልገው ጊዜ እርዝመት ወይም መጠን በላይ መስጠት ያስከትላል፡፡ (የአእምሮ ህክምና ከአማኑኤል በተጨማሪ በጥቁር አንበሳ፣ ዘውዲቱ፣ የካቲት፣ ጳውሎስ እንዲሁም በግል የአእምሮ ህክምና ተቋማት ይሰጣል፡፡ )
3. ቅር የተሰኙ ታካሚዎችና "ዝምተኞቹ ብዙሀን"
ከህክምና የተጠቀሙ ሰዎች በይፋ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሲናገሩ በብዛት አይስተዋልም፡፡ በተለይ እንደ አእምሮ ህመም አድልዎና መገለል ሊያስከትል የሚችል ህመም ሲሆን ዝምታን ይመርጣሉ፡፡ ብዙሃን ቢሆኑም ዝምተኛ ስለሆኑ ገጠመኛቸው አልተሰማም፡፡ ቅር የተሰኙ ታካሚዎች በአንፃሩ ቅሬታቸውን ለመግለፅ ብሎም ሌሎች እንደነሱ እንዳይሆኑ በማሰብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ቅሬታቸውን ይገልፃሉ፡፡ በአብዛኛው ከሚገባው በላይ የሆነ መድሃኒት የተሰጣቸው ወይም መድሃኒቱ የጎንዮሽ ጉዳት ያስቸገራቸው ናቸው፡፡ቅሬታቸውን መግለፃቸው ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ግን "የአማኑኤል መድሃኒት" ለሁሉም ታካሚ መጥፎ እነደሆነ መደምደም ሁሉንም ያማከለ አይደለም፡፡ የአእምሮ መድሃኒቶች ለሁሉም ሰው ተመሣሣይ መጠን የላቸውም፡ የሚያመጡት የጎንዮሽ ጉዳትም ለሁሉም ሰው አንድ አይነት አይደለም፡፡ ልክ ቀዝቃዛና ሙቅ ውሃ እንዳለው ሻወር ለአንድ ሰው የሚስማማውን መጠን ማመጣጠን ይፈልጋል፡፡
ስለ አእምሮ ብዙ ያልታወቁ ነገሮች አሉ፡፡ የአእምሮ ህመምን ለማዳን ብሎም ከጅምሩ ለመከላከል የሚያስችሉ ተስፋ ሰጪ ምርምሮች እየተካሄዱ ነው፡፡ ሆኖም ሁሉም ነገር ስላልታወቀ የአእምሮ ህክምና አያስፈልገም ብሎ መደምደም ስህተት ነው፡፡ (It is commiting the fallacy of argumentum ad ignorantiam)
የአእምሮ ህክምና መድሀኒቶች ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ "ዝምተኛ ብዙሀንን" ስራቸውን በአግባቡ እንዲሰሩ፣ ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ቤታቸውን በሚፈልጉት መንገድ እንዲመሩ እያገዙ ነው፡፡ ሆኖም አሁን ያለው የአእምሮ ህክምና በብዙ ደረጃዎች ክፍተት አሉበት፡፡ ለማሻሻል የሁላችንንም ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡
Comments
Post a Comment