The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
ረጅም ጊዜ ትዳር ውስጥ የቆዩ ሰዎች የሆነ ጊዜ ላይ ለረጅም ጊዜ ያለ ሴክስ ሊቆዩ ይችላሉ፡፡ በፊት በየቀኑ ወይም በሁለት ቀን አንዴ የነበረው ቀስ በቀስ ወደ ሳምንታት ከዚያም ወደ ወራት ሊዘልቅ ይችላል፡፡
በጣም አልፎ አልፎ ወይም ምንም ሳያደርጉ ደስተኛ ሆነው የሚኖሩ የተወሰኑ ባለትዳሮች አሉ፡፡ የሚበልጡት ግን አንዳቸው ወይም ሁለቱም ደስተኛ ሳይሆኑ የሚከሰት ነው፡፡
ከአምስቱ የፍቅር ቋንቋዎች ለአካላዊ ንኪኪ ቦታ የሚሰጡ ሰዎች ለረጅም ጊዜ ሴክስ አለማድረግ የአለመፈለግ ስሜት ይፈጥርባቸዋል፡፡ (ስለ አምስቱ የፍቅር ቋንቋዎች ከዚህ በፊት ቀርቧል፡፡) የሚሰማቸውን ስሜትና ሀሳብ ለመግለፅ ሀፍረት ስለሚሰማቸው ዝም ይላሉ፡፡ ዝምታው ሁለቱም ተጣማሪዎች የየራሳቸውን ግምት እንዲወስዱ ያደርጋቸዋል፡፡ (አንዳንድ ጊዜ አደገኛ የሆኑ ግምቶችን) ይህ ደግሞ ደስተኛ አለመሆን፣ መነጫነጭ፣ እንደ ባልና ሚስት ሳይሆን እንደ ደባል መተያየት የመጨረሻ ደረጃ ሲደርስ ደግሞ ፍቺ ሊያስከትል ይችላል፡
የሴክስ ፍላጎት በጊዜና በሁኔታ ከፍ ዝቅ የሚል ነገር ነው፡፡ ብዙ ነገሮችም ይወስኑታል፦ እርግዝና፣ ልጅ መውለድ፣ የስራ ጫና፣ አካላዊ ጤንነት...ወዘተ፡፡ በግልፅ ፍላጎትን፣ ፍርሀት፣ ስጋትን መነጋገር ጥሩ ነው፡፡ ቢቻል ንግግሩ ከመኝታ ቤት ውጨ በተረጋጋ ሁኔታ ቢደረግ ይመረጣል፡፡( መኝታ ቤት ወይም ከሴክስ በኃላ የሚደረጉ ውይይቶች በስሜት የሚደረጉ ስለሚሆኑ ከመፍትሄ ይልቅ ስሜትን የሚጎዱ መወቃቀሶችን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡)
መኝታ ቤት የሚኖረው መግባባት ከመኝታ ቤት ውጭ ያለውን መግባባት እንደሚወስነው ከመኝታ ውጭ ያለው መግባባት የመኝታ ቤቱን መግባባት ይጨምረዋል፡፡ በተቃራኒውም ደግሞ እውነት ነው፡፡
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment