The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
የቁማር ሱስ ያለባቸው ሰዎች የሚስቡበት መንገድ በጥቂቱ፦
- ሲያሸንፉ በችሎታ ነው፤ ሲሸነፉ በእድል ነው፡፡ ችሎታ የሚያስፈልጋቸው የቁማር ጨዋታዎች አሉ፡፡ እንደ ፑል ወይም አንዳንድ የካርታ ጨዋታዎች፡፡ ወይም እውቀት የሚፈልጉ ውርረዶች እንደ የስፓርት ውድድሮች፡፡ ነገር ግን የፈለገ ችሎታ ቢጠይቁ ሁሉም የቁማር ጨዋታዎች እድል ይፈልጋሉ፡፡ ማሸነፍም መሸነፍም ውስጥ ከችሎታ በተጨማሪ( አንዳንድ ጨዋታዎች ላይ ሙሉ በሙሉ) እድል አለ፡፡ የቁማር ሱስ ያለባቸው ሰዎች ግን ሲያሸንፉ በችሎታ ሲሸነፉ ግን በእድል እንደሆነ ነው የሚያስቡት፡፡
- መርጦ ማስታወስ፦ የቁማር ሱስ ያለባቸው ሰዎች ያሸነፉባቸውን ጥቂት ጨዋታዎች ጥርት አድርገው ሲያስታውሱ የተሸነፉባቸውን ብዙ ጨዋታዎች ይረሳሉ፡፡ በተጨማሪም 'ለጥ..ቂት!' የተሸነፉትን እንዳሸነፋ አድርገው ነው የሚያስታውሱት፡፡ ይህ የወደፊቱን ጨዋታ የማሸነፍ እድላቸውን ሲያሰሉ በተዛባ መንገድ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
- ዞሮ ዞሮ የተበሉትን ያስመልሳሉ፦ የተወሰነ ጨዋታ ቢበሉም ቁማሩን ከፍ ባለ ገንዘብ እስከቀጠሉ ድረስ የተበሉትን እንደሚያስመልሱ ያስባሉ፡፡ በዚህ ምክኒያት ለሌላ ሰው የሚያስደነግጥ ብር እየተበሉም ምንም አይመስላቸውም፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ከተሸነፉ እድል ወደ እነሱ እንደምታዘነብል ያምናሉ፡፡ (they commit Monte Carlo fallacy) ልክ አንድ ልጅ ሲወለድ ሴት ወይም ወንድ የመሆን እድሉ ግማሽ ለ ግማሽ ቢሆንም ከዚህ በፊት ሁለት ሴቶች መውለድ የሚቀጥለውን ወንድ የመሆኑን አድል የሚጨምረው እንደሚመስላቸው ሰዎች፡፡
ለማጠቃለል የቁማር ሱስ ከመቶ ሁለት ሶስት ሰው ላይ ሊከሰት የሚችል የአእምሮ ህመም ሲሆን አብዛኛዎቹ የቁማር ሱስ ያለባቸው ሰዎች በተጓዳኝ ሌሎች ሱሶች ይኖራቸዋል፡፡ በአእምሮ ህክምና ተቋማት ሊታከም ይችላል፡፡
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment