The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
(1) ከአስር አመት በፊት ነው፡፡ ብዙ አቅዶ ሀገር አቋርጦ የሚሄድ መኪና አደጋ ያጋጥመዋል፡፡ ያልተጠበቀ ነው-ግራ የሚያጋባ፡፡ ምክኒያት ሲባል-የትራፊክ(ፖሊስ) ልብስ የለበሰ ሴጣን (ዳቼ) ሹፌሩን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ መርቶት ነው፡፡
(2)ወጣት ነው፡፡ ከሰው ተግባቢ ነው-በትምህርቱ ጎበዝ፡፡ ከጊዜ በኃላ የፀባይ መለዋወጥ፣ ያልተለመደ ንግግር ይታይበታል፡፡ ምክኒያት ሲባል- ጓደኞቹ ደብተሩን ወስደው ድግምት አሰርተውበት ነው፡፡
(1) እንደተባለው አይነት የትራፊክ ልብስ የሚለብስ ሴይጣን ይኑር አይኑር በርግጠኝነት ማወቅ አንችልም፡፡ ቢኖር እና አንደተባለው ቢያደርግ እንደ ሰው ብዙ ልናደርግ የምንችለው ነገር አይኖርም፡፡ ምናልባት .....
የአሽከርካሪ ብቃት፣ የመኪናው የቴክኒክ ሁኔታ ወይም የመንገዱ ሁኔታ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ ሊጠገን የሚችል መኪና፣ ሊስተካከል የሚችል መንገድ፣ ሊሻሻል የሚገባው የአሽከርካሪ ብቃት ሳይደረግ ቀርቶ ሰው ላይ አደጋ ሲደርስ ያሳዝናል፡፡
(2) አንደተባለው በደብተር ተሰርቶ ይሁን አይሁን ማረጋገጥ ከባድ ነው፡፡ ተሰርቶ ከሆነም ለመርዳት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ምናልባት.....
በስነ ህይወታዊ (biological) ፣ ስነ ልቦናዊ (psychological) ወይም ማህበራዊ (social) ሁኔታዎች ምክኒያት የመጣ ከሆነ የምናደርገው ነገር ይኖራል፡፡ በጊዜ በቀላል ህክምና ሊታከም የሚችል ህመም በግለሰቡ፣ በቤተሰቡ እንዲሁም በማህበረሰቡ ላይ ጫና ሲፈጥር ያሳዝናል፡፡
በአጠቃላይ (1)ለመንገድ ደህንነት ተኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
(2)አብዛው የአእምሮ ህመም በጊዜ ከታከሙ ውጤቱ ጥሩ ነው፡፡
ያለ አእምሮ ጤና ጤና የለም፡፡
Comments
Post a Comment