The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
መኪና መንዳት ስንለማመድ ይሁን አዲስ ቋንቋ ስንማር አዲስ አፕሊኬሽን ስንጠቀም ይሁን አዲስ ስራ ስንጀመር በተመሳሳይ የምናልፍባቸው አራት ደረጃዎች አሉ፡፡
- አለማወቅን አለማወቅ፦ በዚህ ደረጃ ላይ ስንሆን ስለነገሩ ግንዛቤ ስለሌለን አለማወቃችንን እንኳ ልናውቅ አንችልም፡፡ ብስክሌት አይቶ የማያውቅ ልጅ ብስክሌት መንዳት እንደማይችል እንደማያውቀው ማለት ነው፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ የሚኖረው ስሜት የአላዋቂ ደስታ ነው፡፡
- አለማወቅን ማወቅ፦ በፊት ከማናቀው ነገር ጋር ከተዋወቅን በኃላ የመጀመሪያዎቹ ሙከራዎች ስኬታማ አይሆኑም፡፡ (በምሳሌ እንደምትጠቀሰው ከበሮ) አለመቻልን መገንዘብ የሚፈጥረው ጭንቀት አለ፡፡ ይህንን ጭንቀት መቋቋም የማይችሉ አዲስነገር መማር፣መልመድ ወይም ማወቅ እዚህ ጋር ያቆማሉ፡፡
- ማወቅን ማወቅ፦ ልክ ብስክሌት መንዳት ስንለምድ ስለፔዳል እያሰብን እንደምንነዳው ወይም አዲስ ሀላፊ ስንሆን መመሪያ አገላብጠን እንደምንወስነው ማለት ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ላይ አዲስ ነገር በመቻል ምክኒያት የሚመጣ ደስታ 'ምናልባት' ከሚል ፍርሀት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ይመጣል፡፡
- ማወቅን አለማወቅ፦ በዚህ ደረጃ ላይ ሲደረስ አዲሱ ነገር ከተፈጥሮአችን ጋር ስለሚዋሀድ እናደረገዋለን እንጂ አናስበው፡፡ ልክ አንድን ቋንቋ በደንብ ስንችል ቃላት ሳንመርጥ ስለ ሰዋሰው ሳንጨነቅ እንደምንናገው ማለት ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ብስክሌት የሚነዳ ለምሳሌ የሚሄድበት ቦታ ሲደርስ ምን እንደሚያደርግ እንጂ ስለመሪ እና ፔዳል አያስብም፡፡
አምስተኛው ደረጃ የሚሆነው ሌላ አዲስ ነገር ለመማር፣ ለመልመድ እና ለማወቅ ከላይ የተጠቀሱትን እንደገና መጀመር ነው፡፡
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment