The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
አደጋዎች ሲያጋጥሙ አካላዊ ጉዳቶች ግልጽ ስለሆኑ ምን መደረግ እንዳለበት አያጠያይቅም፡፡ በግልጽ የማይታዩት የህሊና ቁስሎችስ? የስነ ልቦና ጠባሳዎችስ? ሰው ሰራሽም (የትራፊክ አደጋ፣ የሽብር ጥቃት፣ ጾታዊ ጥቃት...) ሆነ ተፈጥሯዊ ( ጎርፍ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ...) አደጋዎች በራሳችን ወይም በጣም የቅርብ ሰዎቻችን ላይ ሲደርሱ ሁለት መሰረታዊና ተያያዥ እምነቶቻችንን ይንዳሉ፡፡
የመጀመሪያው የሚናደው በህይወታችን የሚከሰቱትን ነገሮች መገመት መቻል ነው፡፡ ስንወጣ እንደምንመለስ፣ ስንሰራ እንደምናገኝ፣ 'ቻው' ስንል ቆይተን እንደምንገናኝ...ወዘተ ሁለተኛው በህይወታችን የሚፈጠሩትን ነገሮች ከሞላ ጎደል መቆጣጠር መቻል ነው፡፡ ለሰው መልካም ካሰብን ሰውም ለኛ መልካም እንደሚያስብ፣ ከተጠነቀቅን አደጋ እንደማይደርስብን፣ ፊት ካልሰጠን ማንም እንደማይዳፈረን...ወዘተ
የነዚህ ሁለት እምነቶች በድንገት መናድ የባዶነት ስሜት፣ ፍርሀት፣ ጭንቀት፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ቅዠት፣ ብቸኝነት ማብዛት፣ ተጠራጣሪ መሆን...ሊያስከትል ይችላል፡፡ የድህረ አደጋ ሰቀቀን ከአደጋ በኃላ የሚፈጠር የስሜት፣ የሀሳብ ፣ የፀባይ ለውጦችን የሚያካትት ነው፡፡ የድህረ አደጋ ሰቀቀን በአደጋው ወቅት ደንግጠው ወይም ግራ ተጋብተው የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ላይ ከጊዜ በኃላ ሊጀምር ይችላል፡፡ በሽብር ጥቃት ስነ ልቦናዊ ጫና ሊደርስ የሚችለው በአደጋው የተጎዱ ሰዎችና ቤተሰቦቻቸው ላይ ብቻ ሳይሆን ሁኔታውን የተመለከቱ እንዲሁም የመጀመሪያ እገዛ ያደረጉ ሰዎች ላይ ጭምር ሲሆን የአእምሮ ሀኪም ወይም የስነ ልቦና ባለሞያ ጋር በመሄድ ሞያዊ እርዳታ ማግኘት ይቻላል፡፡
ከአደጋ በኃላ የሚደርሰውን ስነ ልቦናዊ ጫና ለመከላከል ርብርብ ያስፈልገዎል፡፡ 'ድብቅ ነው' ማለት 'የለም' ማለት አይደለም፡፡
መልካም ጊዜ
Comments
Post a Comment