The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
የአእምሮ ህመምን ማከም እንደሚያስፈልገው ሁሉ የአእምሮ ጤናን ማጎልበት፣ የሰዎች ድክመት ላይ ከማተኮር ጥንካሬያቸው ላይ ማተኮር፣ ጥሩ ያልሆኑትን ለማቅናት የሚሞክረውን ያህል ምርጥ የሆኑትን አንዲያድጉ ማገዝ የአዎንታዊ ስነልቦና ትኩረቶች ናቸው፡፡ የሰው ልጆችን ኑሮ በተሟላ እና በተመጣጠነ መልኩ ለመረዳት ይሞክራል፡፡ "ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዴት መፍታት ይችላሉ?" ከሚለው መደበኛው የስነ ልቦና ሀሳብ በተቃራኒው የቆመ አይደለም፡፡ በአንጻሩ የተለመደውን ስነ ልቦና የሚያግዝና አድማሱን የሚያሰፋ ነው፡፡ ሰዎች ከውልደት እስከ ሞት የሚያልፉባቸውን ሂደቶች ያጠናል፡፡ ሰዎች መሆን የሚችሉትን 'ምርጡን እራሳቸውን' እንዲሆኑ እንዲሁም የሚያደርጓቸውን ነገሮች በተሻለ መንገድ ማድረግ እንዲችሉ ያግዛል፡፡
በህይወት ውስጥ ጥሩ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ በዛው ልክ መጥፎ ነገሮችም አሉ፡፡ የአዎንታዊ ስነ ልቦና ዋነኛ እሳቤው 'ጥሩ ህይወት' ውጣ ውረድን ከማለፍና ችግሮችን ከመቋቋም ከፍ ያለ መሆን አለበት የሚል ነው፡፡
ሰዎች በራሳቸው መንገድ ደስተኛ የሚያደርጋቸውንና በህይወታቸው የሚሰማቸውን እርካታ የሚወስኑ ነገሮችን ሲጠየቁ የሚሰጧቸው ምላሾች በሚያስገርም ሁኔታ ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ከአሜሪካ ሚሊየነሮች እስከ የህንድ ጎዳና ተዳዳሪዎች የሰጧቸው ምላሾች ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ቀጥለው የተዘረዘሩት ዘር ፣ ፆታ፣ የትምህርት ደረጃ ሳይለዩ ከደስታና ከአእምሮ ጤንነት ጋር ከፍተኛ ተያያዥነት አላቸው፡፡
** የጓደኞች መኖር
** ትዳር
** ተጫዋች መሆን
** አመስጋኝ መሆን
** ሀይማኖተኛ ሰው መሆን
** መዝናናት
** ስራ( የገቢዉ መጠን የጎላ ልዩነት አያመጣም)
በስራ ቦታ ምርጥ ጓደኛ መኖር( a best friend at work) ሰዎች በጣም ደስተኛ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ በስራቸው ስኬታማ እንዲሆኑ ያስችላል፡፡ ለማጠቃለል ደስተኛ በሆኑና በጣም ደስተኛ በሆኑ ሰዎች ያለው አንድ መሰረታዊ ልዩነት በጣም ደስተኛ የሆኑ ሰዎች የልብ ወዳጅና በጣም ጥሩ ማህበራዊ ህይወት አላቸው፡፡ (ከSynopsis of psychiatry, 11th edition የተተረጎመ)
ህይወት ውጣ-ዉረድን ከማለፍና ችግሮችን ከመቋቋም ከፍ ያለ መሆን አለበት!!!
Comments
Post a Comment