The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
በዓል ሲመጣ ባለትዳሮች ላይ "ማን ጋር ነው የምንሄደው?" የሚል ጥያቄ ይፈጠራል፡፡ በተጨማሪም ብዙ ሰዎች በዓልን ከአማች ጋር ማሳለፍ ያሳስባቸዋል፡፡ ማሳሰቡ ወደ ጫና እንዳይለወጥ የሚያግዙ አና አለፍ ሲልም ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ የሚረዱ አምስት ነጥቦች፦
1. በግልፅ መነጋገር
ቀደም ብሎ የትኛውን በዓል ማን ጋር እንደሚያሳልፉ መነጋገር ጊዜው ሲደርስ የሚፈጠረውን አለመግባባት ያስቀራል፡፡ የትዳር የመጀመሪያዎቹን በዓላት አከባበር የወደፊቱን ልማድ ስለሚወስኑ በጊዜ ተነጋግሮ መወሰኑ የተለያየ ግምት እንዳይኖር ያደርጋል፡፡
2. ቅድሚያ ለትዳር አጋር መስጠት
ለባላቸው/ለሚስታቸው ቅድሚያ የሚሰጡ ጥሩ ትዳር ይኖራቸዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውን የሚወዱና የሚያከብሩ ሲሆኑ ለትዳራቸው ግን ከሁሉም በላይ እንደሆነ ያስታውሳሉ፡፡ አንዳንድ ቤተሰቦች ውስጥ የሰው ትዳር ላይ ጣልቃ የሚገባና አስተያየት የሚሰጥ ሰው ይኖራል፡፡ ባልና ሚስት አንድ እንደሆኑ በማሳየት ክፍተት እንዳይፈጠር ማድረግ ይችላሉ፡፡
3. መቼ እንደምትመለሱ በቅድሚያ መወሰን
አማች ጋር ከመሄድ በፊት ምን ያህል እንደምትቆዩ ለምን መመለስ እንደለባችሁ መነጋገር፡፡ መሄድ ሲኖርባችሁ ተመሳሳይ መልስ መስጠት ያስችላል፡፡ ሌላ ሀገር የምትሄዱ ከሆነ የምታርፉበትን ቦታ በቅድሚያ ማዘጋጀት ጥሩ ነው፡፡( ከአማች ጋር ቢጃማ ለብሰው መገናኘት የማይመቻቸው ሆቴል ቀደም ብለው እንዲይዙ ይመከራል፡፡)
4. አንድ ቀን መሆኑን ማስታወስ
ምንም ይሁን ምን አንድ ቀን መታገስ አይከብድም፡፡ ከተወሰኑ ሰዓታት በኋላ አንደምትመለሱ ማሰብ የተወሰነ መረጋጋት ይፈጥራል፡፡ አማቾች እንዲወዱን መፈለግ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ነገር ግን ጊዜ የሚወስድ ሂደት ነው፡፡ የአሁኑ በዓል በዛ ሂደት ውስጥ አንድ ቀን ብቻ ነው፡፡
5. ተጫዋች መሆን
የፈለገ ብንግባባም አማች ጋር መሄድ ይብዛም ይነስም የሆነ ውጥረት ይፈጥራል፡፡ ዝም ብሎ ተቀምጦ አስር ጊዜ "ተጫወት/ቺ" መባል ውጥረቱን ቢያብሰው እንጂ አይቀንሰውም፡፡ ገጠመኝን ማጋራት፣ ጥያቄ መጠየቅ ሁኔታውን ቀለል ያደርገዋል፡፡ የፈለገ ብንቀራረብ ከጓደኞቻችን ጋር የምናወራቸውን ቀልዶች ልናወራ አንችልም(ምክኒያቱ ግልፅ ይመስላል፡፡) በተቻለ መጠን የጋራ የሆኑና የማየከራክሩ ርዕሶችን ማንሳት ጥሩ ጊዜ እንዲኖር ያደርጋል፡፡
ባጠቃላይ ከትዳር በኋላ በዓል አዲስ መልክ ይኖረዋል፡፡ በግልፅ በመነጋገር ደስተኛ ትዳር፣ ከአማች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲሁም አሪፍ በዓል ማሳለፍ ይቻላል፡፡
መልካም በአል
Comments
Post a Comment