The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
እንትን ምንድነው? ምንን ይወክላል፡፡ በእንግሊዘኛ ተቀራራቢው ቃል 'thingamajig' ቢሆንም የምንጠቀምበት አውድ ግን የተለያየ ነው፡፡
'እንትን' በአብዛኛው በቀጥታ ቢገለጽ በሰዎች ዘንድ ይበልጡኑ ደግሞ በራሳችን ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸውን ነገሮች ለመወከል ይጠቅማል፡፡
ውስጠ አእምሯችን ውስጥ ተከታታይ የሆነ ፍትጊያ የሚያደርጉ አራት ሀይሎች አሉ፡፡ 1. እንስሳዊ ፍላጎት (የሴክስ ወይም የሀይለኝነት) 2. ህሊና 3. በህይወታችን ትርጉም ያላቸው ሰዎች እና 4. ገሀዳዊ እውነታ ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ንግግራችን እና ድርጊታችን አራቱንም ያማከለ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ግን ከአራቱ የተወሰኑት ሊጋጩ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ አእምሮአችን እነሱን ለማስታረቅ(ከኛ እውቅና ውጭ) በሌላ ተቀባይነት ባለው ድርጊት ወይም ቃላት ይለውጠዋል፡፡
እንትን በብዙ ቦታ ሊያገለግል የሚችል ከነዚህ ቃላት አንዱ ነው፡፡ ለምሳሌ ተገቢ ያልሆነ አገልግሎት መስሪያ ቤት የሚጠይቅ ሰው ጉዳዩን በአቋራጭ መጨረስ ቢፈልግም ህሊናው ከሞገተው ቢሮ ሀላፊውን ገብቶ ሳያስበው "እንትን ፈልጌ ነበር " ሊል ይችላል፡፡
ጓደኞቹ ሁሉ ሁሉ የአንድ ቡድን ደጋፊ ሆነው እሱ ብቻውን የሌላ ቡድን ደጋፊ ከሆነ " የእንትንን ጨዋታ ላይ ልሄድ ነው፡፡" ሊል ይችላል፡፡ እውነታው ከህሊናው ጋር አይጋጭም ነገር ግን በህይወቱ ትርጉም ካላቸው ሰዎች ጋር ስለሚጋጭ፡፡
መንገድ ላይ አንዱ ምስኪን የሆነን ሰው ሲያንገላታ ብናይ እንናደዳለን፡፡ እንስሳዊ ፍላጎታችን ፍትህን በመሰንዘር እንድናስከብር ሊገፋፋን ይችላል፡፡ ነገር ግን በገሀዱ ያንን ማድረግ አንችልም፡፡ ይህን ሰው እንደው አርባ "እንትን..." ልንን እንችላለን፡፡ ወይም ያናድነን ስለነበረ አለቃችን ስናወራ "ያ እንትና " ልንል እንችላለን፡፡
ለማጠቃለል ራስን ማወቅ ብዙ አለማዊ ነገሮችን ከማወቅ የተሻለ ነው፡፡ በቀጣይ "እንትን" የሚለውን ቃል ስንጠቀም ለምን እንዳልን ብናሰላስል ስለራሳችን ያለን ግንዛቤ ትንሽ ከፍ ይል ይሆናል፡፡
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment