The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
አንድ ሴት በፍቅር ጓደኛዋ ወይም በባሏ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲደርስባት "ለምን ትታው አትሄድም?" የሚል ጥያቄ ይፈጥራል፡፡ መልሱ ግን ለጠያቂ እንደሚቀለው አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ አስቸጋሪ ፀባይ ካለው ሰው ጋር የፍቅር ግንኙነት ያላቸው ሴቶች ትዳራቸው እንዳይፈርስ እና ፍቅራቸው እንዲቀጥል የሚለውን መቀበል፣ ፍላጎቱ አንዲሟላ መጣጣር እንዲሁም የሚያምኑባቸውን ነገሮች አስከመተው ይደርሳሉ፡፡ ግን ይሄም በቂ አይሆንም፡፡ ነገር ግን እንደዚህም ሆኖ ትተው ለመሄድ ይቸገራሉ፡፡ ምክንያቶቹ እነሆ፦
1. ተስፋ-
ጥቃት የሚጀምረው ከተወሰነ ጊዜ በኃላ ነው፡፡ (ከመጀመሪያው እንደዚሁ ቢሆን ለውሳኔ ቀላል ይሆን ነበር፡፡) መጀመሪያ አካባቢ ተንከባካቢ፣ አክብሮት ያለው፣ ጥሩ አፍቃሪ ነበረ፡፡ከጊዜ በኋላ የመጣ ስለሆነ፤ ከጊዜ በኃላ እንደበፊቱ ጥሩ አፍቃሪ ይሆናል በሚል ተስፋ ያደርጋሉ ፡፡ በተጨማሪም የበፊቱ የፍቅር ጊዜያት ትዝታ ስላለ ጨክኖ ለመለያየት ይቸገራሉ፡፡
2. ፍርሀት-
ጥቃት የሚያደርሱ ሰዎች ፍቅረኛቸው ልትለያቸው እንደሆነ ሲያውቁ የተለያዩ ማስፈራሪያ ይሰነዝራሉ፡፡ "ልጆቹን እወስዳቸዋለሁ!!" "ቤተሰቦችሽን እንደዚህ አደርጋለሁ!!" "ትተሽኝ የምትኖሪ ይመስልሻል" ...ወዘተ እያሉ ይዝታሉ፡፡አንዳንዶቹ ከዛቻም ያልፋሉ፡፡ እነዚሀ ነገሮች ትታው ብትሄድ ሊፈጠር የሚችለውን በመፍራት እንድትቆይ ያደርጓታል፡፡
3. ማህበራዊ ጫናና ስህተት እንደሆነ አለማወቅ-
ጥቃት የሚያደርሱ ሰዎች ብዙ ጊዜ ሴቷን የተለያየ ሰበብ በመፍጠር ከቤተሰብ ከጓደኛ ይነጥሏታል፡፡ በተጨማሪ ብዙዎቹ ጥቃት የሚያደርሱ ሰዎች "የውጭ አልጋ የቤት ቀጋ" የሚባሉ አይነት ናቸው፡፡ በቤተሰብ በስራ ቦታ በጓደኞቻቸው "ጥሩ ሰው" ስለሚባሉ ጥቃት የደረሰባት ሴት ለማንና እንዴት እንደምትናገር ግራ ይገባታል፡፡ በሌላ በኩል በልጅነቷ አባቷ አናቷን ሲመታ እያየቸ፤ በአካባቢዋ ሴቶች ጥቃት እየደረሰባቸው ተቀብለውት ሲኖሩ አያየች፤ በባህል ዱላ እንደፍቅር መግለጫ ተደርጎ ሲወራ እየሰማች በባሏ ጥቃት ሲደርስባት ስህተት እንደሌለው ልታስብ ትችላለች፡፡
4. የኢኮኖሚ ጥገኝነት-
ሴቶች እንዳይማሩ እንዲሁም በስራቸው እንዳያድጉ የተለያየ ሰበብ እየፈጠሩ የኢኮኖሚ ጥገኛ እንድትሆን የሚያደርጉ ወንዶች አሉ፡፡ ራሷን ለማስተዳደርና ልጆቿን ለማሳደግ የገንዘብ ነፃነት የሌላት ሴት ምንም ሁኔታ ቢፈጠር ተቋቁሞ መኖር እንደ ብቸኛ አማራጭ ሆኖ ይታያታል፡፡
በምንም ምክኒያት በማንኛውም በማንኛውም ሁኔታ ጥቃት ተቀባይነት የለውም!!!
ሴቶች ከጥቃት ነፃ የሆነ ህይወት መብታቸው ነው!!!
Comments
Post a Comment