The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
ማዶና ፑታና ኮምሌክስ ሁኔታዊ (Situaional) ስንፈተ ወሲብ ነው፡፡ ከሚወዷት ፍቅረኛ ወይም ሚስት ጋር ሴክስ ለማድረግ አለመቻልና በተቃራኒው ከሴተኛ አዳሪ ጋር ምንም ስንፈት አለመኖር ሲሆን በተለይ ሚስቶች ልጅ ከወለዱ በኀላ የሚፈጠር ነው፡፡ ይህ ስነ ልቦናዊ ኮምፕሌክስ ያለባቸው ሰዎች የፍቅር ስሜት ላላቸው ሰው የሴክስ ፍላጎት አይኖራቸውም፡፡ የሴክስ ፍላጎት ላላቸው ሰው ደግሞ የፍቅር ስሜት የላቸውም፡፡ሴክስና ፍቅር ሳይዋሀዱ እንደ ዘይት እና ውሀ ሆነው አእምሮ ውስጥ ሲቀመጡ የሚፈጠር ነው።
እነዚህ ሰዎች ሴቶችን ሁሉ በሁለት ይከፍላሉ፡፡ ንፅህት እና ባለጌ፡፡ የሚሰማቸውም ፍቅር በሁለት የተከፈለ ነው፡፡ ንፁህ ፍቅርና የብልግና፡፡ ሚስቶቻቸው ልጅ ከወለዱ በኃላ እንደ ሚስት ሳይሆን እንደ እናት ማየት ይጀምራሉ፡፡
ሴክስ ፎሮይድ እንደሚለው ሁሉንም ፀባይ የሚወስን አይሁን እንጂ ከአካላዊ ድርጊቱ ግን የዘለለ ስነ ልቦናዊ እና መንፈሳዊ ትርጉም ያለው እንደሆነ እርግጥ ነው፡፡ ሴክስ 'ባለጌ ነገር' እየተባለ በሚነገርበት ሁኔታ ውስጥ ማደግ የሚያስከትለው ተፅዕኖ ምን ይሆን?
ሴክስ አብዛኛው ነገሩ የሚካሄደው በእግሮች መሀል ሳይሆን በጆሮዎች መሀል ነው፡፡
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment