The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
በሰባተኛው መልአክ ላይ የተተረከው አየለ ነብር ስኪዞፍሬኒያ የሚባል የአእምሮ ህመም እንዳለበት ማወቅ ይቻላል፡፡ የአእምሮ ህመሙን አስመልክቶ የተፃፈው ሳይንሳዊ ትክክለኛነቱ (Scientific accuracy) ከፍተኛ ከመሆኑ ባሻገር ስለ አእምሮ ህመም ያለንን ማህበረሰባዊ እይታ በደንብ የሚያሳይ ነው፡፡
አየለ ከሰዎች ስለ አእምሮ ህመሙ የተባለውን ሲገልፅ ገፅ 76"...ደግሞ በመታመሜ ሀበሾች በጣም ነው ያፈሩብኝ፣ በጣም ነው የናቁኝ፣ አንተ ባትኖር የሚያሳፍር ይመስለኝ ነበር፡፡ በህመም ላይ እፍረት። ይታይሀል? አንተና ያሲን ብቻ ናችሁ ሁኔታዬን አስጨናቂ ሸክም ነው እንጂ አሣፋሪ ውድቀት አይደለም ያላችሁኝ። ይህ አስተያየታችሁ ብዙ አግዞኛል። ብዙ"
በተጨማሪ ስለ መገለልና መድልዖ ገፅ 68 "...ያሲን ሀበሾችን ታዘባቸው። ሁልጊዜ አንድ ላይ ስለሚያያቸው የሚዋደዱ፣ የሚተዛዘኑ ይመስለው ነበር። አሁን ግን አንድ ላይ የሚታጎሩት ለመለያየትና በየፊናቸው ለመሄድ ባለመድፈራቸው ብቻ መሆኑ እየገባው ሄደ። ፈተና ደርሶብናል እያሉ አየለን ለኛ ጥለውልን ይሄዳሉ፣ ግን ቢያንስ በቀን ሶስት ሰአት ካፌ ውስጥ እያወሩ ወይም ካርታ እየተጫወቱ ማሳለፋቸው አልቀረም፡፡ ታዲያ እኔንና ያሲንን ሲያገኙን ስለ አየለ "ምክር ለበስ ቁም ነገር" ያካፍሉናል፡፡ "ሀኪም ቤት መሄድ አልፈልግም አለ፣ ወይ ጉድ ምን ይሻላል? ምናልባት አንዳንዴ ወደ ገጠር ሽርሽር ብትወስዱት አንጎሉን ሳያድስለት ይቀራል?...ልጁ እንደመክሳት ሳይል አልቀረም። የአሳማ ስጋና ፍራፍሬ ቢበላ ነፍሱን መለስ ያደርግለት ይሆናል እኮ። ሙዚቃ! ለተጨነቀች ነብስ ከሙዚቃ የበለጠ የሰላም መልእክተኛ ከየት ተገኝቶ! ወዘተ። ነገር ግን አየለን ለአንድ ሰአት እንኳ ያጫወተው የለም።"
በአንፃሩ ስብሀት እንደአእምሮ ሀኪም፦ አየለ ስብሃት ሊረዳው እንደሚፈልግ ሲገልፅ ገፅ 75 "...እዚህ ፈረንሳይ የመጣኸው ዲግሪ ፍለጋ ብቻ ሳይሆን፣ ስለሰው ልጅ ፍጥረትና ባህሪ ማወቅ እንደምትፈልግ በግልፅ ይታየኛል፡፡" ስብሃት በበኩሉ ገፅ 85 ላይ "... ፍርሀት መንቀጥቀጡን መቼ ቀመስኩትና ልገስፀው እችላለሁ? ድካሙን መቼ ተሸከምኩለትና ልመክረው እችላለሁ? ዝም አልኩት።" ብሏል፡፡
ስለ ህመሙ መንስኤ፣ መገለጫ እንዲሁም ስነ ልቦናዊ መረዳት የፃፈው እንዲሁም ስለስብሃት ፍሮይዳዊነት(Freudianነተ) በሌላ ጊዜ ይቀርባል፡፡
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment