The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
ፓኒክ በድንገት የሚመጣ ከፍተኛ ፍርሀት ሲሆን አእምሯዊም አካላዊም ምልክቶች አሉት፡፡ ትንፋሽ ማጠር፣ ልብ ቶሎ ቶሎ መምታት፣ ማላብ፣ መደንዘዝ፣ ማቅለሽለሽ "ልሞት ነው?" "አእምሮዬን ልስት ነው?" የሚሉ ሀሳቦች፡፡ ፓኒክ ግፋ ቢል አስር አስራአምስት ደቂቃየሚቆይ ይሁን እንጂ ፓኒክ ያጋጠማቸው ሰዎች ያላሰቡት ቦታ ወይም ሁኔታ ውስጥ ድጋሚ እንዳያግጥማቸው መፍራት እና መጨነቅ ይጀምራሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከቤት ውጭ ፓኒክ እንዳያግጥማቸው በመፍራት ከቤት የማይወጡ ሰዎች አሉ፡፡ ለዚህ ነው ፓኒክ ዲስኦርደር "የፍርሀት ፍርሀት" የሚባለው፡፡
ፓኒክ ዲስኦርደር ከመቶ ሰው ከአንድ እስከ አራት ሰው ላይ ሊከሰት የሚችል ሲሆን ሴቶች ላይ የመከሰት እድሉ ከወንዶች ይልቅ ሁለት እጥፍ ነው፡፡ የፓኒክ ዲስኦርደር መንስኤዎች ብዙ ሲሆኑ በባህሪያቸው የሚጨነቁ እና ጭንቀት ጎጂ ነው ብለው በሚያስቡ ሰዎች ላይ ይጨምራል፡፡ በተጨማሪም የህይወት ጫና፣ ከሚወዱት ሰው አለመግባባት ወይም መለየት ሊቀሰቅሱት ይችላሉ፡፡ ፓኒክ ዲስኦርደር ያለባቸው ብዙዎቹ ሰዎች ቡና ሲጠጡ የመጨናነቅ ስሜት ይሰማቸዋል፡፡
የፓኒክ ምልክቶች አካላዊ ስለሆኑ ታካሚዎች ወደ የውስጥ ደዌ ወይም የልብ ስፔሻሊስት ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ በምርመራ ግን የሚገኝ ነገር አይኖርም፡፡ ፓኒክ ዲስኦርደር ውጤታማ በሆነ ሁኔታ በንግግር ህክምና ወይም በመድሀኒት ሊታከም ይችላል፡፡
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment