The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
ማስቲሽ ወይም ቤንዚን ከሌሎቹ ሱስ አምጪ ነገሮች በተለየ በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉ፣ ውድ ያልሆኑና ህገ ወጥ ያልሆኑ ናቸው። እነዚህ ሶስት ምክኒያቶች እድሜያቸው ለጋ በሆኑና ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ በሚገኙ ልጆች እንዲዘወተሩ አድርጓቸዋል። ለዚህ ድርጊት የሚውሉት የተለያዩ ነዳጆች፣ ማስቲሽ፣ የሚነፉ ቀለሞች ፣ ጥፍር ቀለም ማስለቀቂያዎች እና የተለያዩ የቀለም ማቅጠኛዎች...ወዘተ ናቸው፡፡
የሚሳቡት ኬሚካሎች አንዳንዶች ላይ 'ለቀቅ' የማለት እና የነውጠኝነት ስሜት፣ ሌሎች ላይ ድክምክም ማለት ይፍጠሩ እንጂ በተደጋጋሚ እንዲወሰዱ የሚያደርጋቸው ለተወሰነ ጊዜ የሚቆየው 'የመንሳፈፍ አይነት ደስታ' ነው። ከፍ ባለ መጠን ከተወሰደ የፍርሀት ስሜት፣ የሌሉ ድምጾች መስማት እንዲሁም ለረጅም ጊዜ ሲወሰድ የአእምሮ እድገትና በተለይ የማስታወስ ችሎታ ላይ ጉዳት ያደርሳል፡፡
በሌሎች ሀገራት የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ይህ ችግር በታዳጊዎች ላይ በይበልጥ እንደሚታይና ለመከላከል የሚረዱ ስርአቶች እንዳሏቸው ነው፡፡ በሀገራችን የተሰራ ጥናት አላገኘሁም፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩ ስለመኖሩ ቁጥሮች ባይገኙም የአዲስአበባ ዋና ዋና ጎዳናዎች ግን ይመሰክራሉ፡፡ ትኩረት እንደሚፈልግ አያጠያይቅም!
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment