The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
ዘመናዊነት፣ ትምህርት፣ፍትህ ከአዲስ የማሰቢያ መንገድ ውጭ ምንድናቸው? የሰው ልጆች እጅግ አስደናቂ ችሎታችን ማሰብ ከመቻላችን በላይ ስለማሰብ ማሰብ መቻላችን ነው፡፡ ስለማሰብ ማሰብ የምናስብበትን መንገድ ለማሻሻል ከማስቻሉም በላይ ሌሎች ሰዎችን በተሻለ ለመረዳት ያስችላል፡፡ ስለምናስበበት መንገድ አብዝተን ባሰብንና ስለሀሳቦቻችን የተረዳነውን ተግባር ላይ ስናውል የበለጠ ደስተኛ የበለጠ ውጤታማ እንሆናለን፡፡
ሀሳባችን እውነታውን ሊወክልም ላይወክልም ይችላል፡፡ "እኔ ያሰብኩት ነው እውነታው!" ብሎ ክችች ማለት ስለማሰብ እያሰብን እንዳልሆነ ያሳያል፡፡ በእንግሊዘኛው Psychic equivalence ይባላል፡፡ምናባችንን ወደ እውነታው ከማምጣት እውነታውን ወደ ምናባችን ለማምጣት እንደመጎተት ነው፡፡ ሀሳባችን ማለት ሙሉ ለሙሉ እኛን አይወክልም፡፡ ሀሳባችን የኛ እንጂ እኛ አይደለም፡፡
ስለማሰብ ማሰብ የአስተሳሰብ ስህተቶቻችንን መለየት፣ ጠቃሚ የሆኑትን ማጠናከር እና ሂደቱን በተከታታይ ማስተዋል ነው፡፡ የንግግር ህክምና(Psychotherapy) በቀላሉ ሲገለፅ ሰዎች ከሀሳባቸው ትንሽ ወደ ወደ ኃላ ብለው ሀሳባቸውን በራሳቸው መመርመርና መለወጥ እንዲችሉ ማገዝ ነው እንጂ ብዙዎች እንደሚመስላቸው ሰዎችን መምከር አይደለም፡፡
አስተሳሰባችንን ስንለውጥ የየራሳችን ትንሿን አለማችንን መለወጥ እንችላለን፡፡
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment