The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
እርጅና ሲመጣ የሰዎች ትኩረት ከገንዘብ ወደ ጤንነት ይዛወራል፡፡ በጉልምስና ወቅት ብዙ ሰዎችን የሚያሳስባቸው ከሰው ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት እና ስራ ሲሆን በእርጅና እድሜ የሚከሰተውን አካላዊ ለውጦች ወይም ህመሞችን ተከትሎ የሚያሳስባቸው በይበልጥ አካላዊ ሁኔታ ነው፡፡
በእርጅና እድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ሰባት ተጨማሪ አመታት የሚኖሩ ሲሆን አንድ አያት ብቻ ካለን ብዙ ጊዜ ሴት አያት ነው የሚኖረን።
በእርጅና እድሜ የሚጠበቁ ነገሮች፦
- ህይወትን ዞር ብሎ መቃኘት
- ከቁሳዊ ነገሮች ጋር ያለ ቁርኝት መቀነስ
- የትዳር አጋር/ ጓደኞችን ማጣት የሚፈጥረውን ሀዘን መቋቋም
- ከጡረታ ጋር የተያያዙ ለውጦችን መቀበል
- ከልጅ ልጅ ጋር የሚኖር ግንኙነት...ወዘተ
እንደ ኤሪክሰን በእርጅና እድሜ ላይ ሰዎች ያለፉበትን ይቃኙና ባሳለፉት ህይወት ደስተኛ ከሆኑ እርካታና ሰላም ይሰማቸዋል፡፡ በተጨማሪም ሞትን በፀጋ ለመቀበል ዝግጁ ናቸው፡፡ "ሞት ሆይ መውጊያህ የታለ የሚሉ ይመስላል፡፡"በአንፃሩ ህይወት አጭር እንደሆነ፣ በህይወታቸው ትክክለኛ ውሳኔ እንዳልወሰኑና ለማስተካከል ጊዜ እንደሌላቸው የሚያስቡ ከሆነ ውጤቱ መበሳጨት እና ንጭንጭ ይሆናል፡፡
"አርባ አመት ለወጣቶች የእርጅና እድሜ ሲሆን ለሽማግሌዎች ሀምሳ አመት የወጣትነት እድሜ ነው፡፡" ቪክቶር ሁጎ
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment