The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
ጭንብል ብዙ አይነት ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዶቹ ግልፅ እና አካላዊ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ግልፅ ያልሆኑ የስብእና ናቸው፡፡ ሁሉም ጭንብሎች ሁለት መሰረታዊ አገልግሎት አላቸው፡፡ ማሳየት የማንፈልገውን መሸፈን እና ማሳየት የምንፈልገውን ማጉላት፡፡ የአእምሮ ህክምና ከስብእና ጭንብል ጋር የሚዋሰንበት ድንበር ሰፊ ነው፡፡ ጥቂት ምሳሌዎች፦
ሀርቬይ ክሊክለይ ሳይኮፓቶችን ሲገልፅ "እነዚህ የ ጤነኛ/ደህና ሰው የሚያስመስል ጭንብል የለበሱ ከጭንብሉ ስር ግን አዎንታዊ ስሜቶች (ፍቅር፣ ርህራሄ፣ ደግነት..) የሌላቸው በተቃራኒው አሉታዊ ስሜቶች (ምቀኝነት፣ ብስጭት፣ ቂም...) የሚተራመሱባቸው ናቸው፡፡" ብሏል፡፡
ካርል ዩንግ ሁላችንም ወክለን የምንጫወተው ምስለ'ኔ እንዳለን ይተነትናል፡፡ ሁላችንም መሆን በምንመኘው እና በእውነታው መካከል ያለውን ልዩነት በምስለ'ኔ ለመሙላት እንሞክራለን፡፡
በሁሉም ቦታ፣ በሁሉም ሁኔታ እውነት ሁሉም ሰው የሚፈልገው ነገር አይደለም፡፡ ለምሳሌ "ስብሰባው ለይስሙላ ነው እንጂ ለውጥ እንዲመጣ ታስቦ የተዘጋጀ አይደለም፡፡" ለማለት አስቸጋሪ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ ወይም አማቻችንን "በዚህ እድሜዎ ሂውማን ሄር ከሚያደርጉ የተፈጥሮ ፀጉርዎ የተሻለ ይመስለኛል፡፡" አንልም፡፡ በማንኛውም ሁኔታ ውሸት ጉንጫችንን ከምትስመን እውነት በጥፊ ብታጮለን የምንመርጥ ስንቶቻችን እንደሆንን እኔ'ነጃ፡፡
አልፎአልፎ በሁኔታዎች አስገዳጅነት ከሆነ ማህበራዊ ትስስር እንዳይላላ ይረዳል፡፡ጭንብል ከተደጋገመ ግን እውነት ይመስልና እውነተኛውን እና ጥልቅ ማንነታችንን እየተውን ጭንብሉን እየመሰልን እንመጣለን፡፡
ፌስ ቡክ ላይ የሚፓሰቱት ምስሎች የሚያሳዩት ሰዎች ሁሉ በብዛት እንደሚዝናኑ፣ ብዙ ጊዜ እንደሚዘንጡ፣ መልካም/ዘና የሚደርጉ ሀሳብ እንዳላቸው፣ኢፍትሀዊ ድርጊት ሀሳብ እንደሚቃወሙ ...ወዘተ ነው፡፡ የራሴን ፌስቡክ ስመለከትም ተመሳሳይ ነው፡፡በእውነታው የምንኖረው ፌስቡክ ላይ ካለው 'ትንሽ' ይለያል፡፡
ጭንብል ደካማ ጎናችንን በመሸፈን ለአደጋ የመጋለጥ እድላችንን ይቀንሰዋል፡፡ ድክመታችንን መገንዘብና መቀበል ግን እውነተኛ ጓደኛ እንዲኖረን፣ የህይወት ግባችንን እንድንለይ፣ ልዩ የሆነውን እምቅ አቅማችንን እንድናወጣ እና ራስን በመሆን ነፃነት ውስጥ የሚገኘውን ደስታ ያላብሰናል፡፡
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment