The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
ፈገግተኛ ዲፕረሽን ከተለመደው ዲፕረሽን ወጣ ያለ ሲሆን እነዚህ ሰዎች የሚሰማቸውን መከፋት፣ ተስፋ ማጣት...ወዘተ በውስጣቸው ይዘው በአብዛኛው ፈገግታ የሚታይባቸውና በሌሎች ሰዎች እንደ ደስተኛ የሚታዩ ናቸው፡፡ በአብዛኛው ትዳር/የፍቅር ጓደኛ፣ ስራ አላቸው፡፡ በስራቸው ስኬታማ፣ በማህበራዊ ኑሯቸው ጥሩ ይሁኑ እንጂ ለብቻቸው ሲሆኑ ተስፋ መቁረጥ፣ መሰላቸት፣ የእንቅልፍ ችግር ያጋጥማቸዋል፡፡
ዲፕረሽን ሁሉም ሰው ላይ በተመሳሳይ የሚገለፅ ህመም አይደለም፡፡ ስራውን እየሰራ ስለሆነ ግለሰቡ ራሱ ዲፕረሽን እንዳለበት ላይረዳ ይችላል፡፡ፈገግተኛ ዲፕረሽን ከዲፕረሽን የባሰ የሚያደርገው ዲፕረሽን ያላቸው ሰዎች ራስን የማጥፋት ሀሳብ ቢኖራቸውም ለመሞከር አቅም ስለማይኖራቸው ራስን የማጥፋት እድላቸው(በንፅፅር)ዝቅ ያለ ነው፡፡ በእምነት ጠንካራ መሆንና የልጆች መኖር ራስን ከማጥፋት በከፍተኛ ደረጃ የሚከላከሉ ይሁኑ እንጂ መቶ ከመቶ ያስቀሩታል ማለት አይደለም፡፡
አንዳንድ ፈገግተኛ ዲፕረሽን ያለባቸው ሰዎች ዲፕረሽንን እንደ ድክመት ስለሚያዩት ሞያዊ እርዳታ ለማግኘት ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡ በአጠቃላይ መከፋትን በተመለከተ በጣም አስፈላጊ ነገር ስሜትን መናገር መቻል ነው፦ለጓደኛ፣ ለቤተሰብ እንዲሁም ሞያዊ እገዛ የሚያስፈልግ ከሆነ ከስነ ልቦና ባለሞያ ወይም ከአእምሮ ሀኪም ጋር መነጋገር ጥሩ ነው።
ፈገግተኛ ዲፕረሽን ላይ በብዛት ከሚከሰቱ ስሜቶች አንዱ ብቸኝነት ሲሆን ብቻዎን እንዳልሆኑና ዲፕረሽን ውጤታማ በሆነ መልኩ ሊታከም የሚችል ህመም መሆኑን ማስታወስ ጥሩ ነው፡፡
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment