The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
ጎረምሶች አካላቸው ከፍ ያለ ህፃናት ናቸው? ወይስ አእምሯቸው ያልበሰለ 'ትልቅ ሰዎች'? ጉርምስና የሚጀምረው በአካላዊ ለውጦች ሲሆን ስነ ልቦናዊ ለውጦቹ በኃላ የሚመጡ ናቸው፡፡ አካላዊ ለውጦቹ ስለ ራሳቸው አብዝተው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል፡፡ አንዳንዶች ላይ ብጉር፣ የድምፅ መቀየር እና ሌሎች አካላዊ ለውጦች የተዘባ አካላዊ እይታ በዘለቄታው እንዲኖራቸው ሊያደርግ ይችላል፡፡ በተጨማሪም አብዛኛው ሶሻል ፎቢያ የሚጀምረው በአስራዎቹ እድሜ ውስጥ ነው፡፡
ጉርምስና የቤተሰብ ልጅ ከመሆን በራስ ሰው ወደ መሆን የሚደረግ ሽግግር በመሆኑ ብዙ ጊዜ ከቤተሰብ ጋር አለመግባባት ይስተዋልበታል፡፡ በጉርምስና እድሜ ላይ ለሚገኙ ታዳጊዎች በአለም ላይ እጅግ አስፈላጊው ነገር በእኩዮቻቸው /ጓደኞቻቸው እይታ ተፈላጊ ወይም "cool" መሆን ነው፡፡ አንዳንዶቹ በቤተሰባቸው ጣልቃ ገብነት እፍረት ይሰማቸዋል፡፡ ብዙ በዚህ እድሜ ላይ የሚገኙ ታዳጊዎች ልዩ እንደሆኑና ማንም እንደማይረዳቸው ያስባሉ፡፡
በጉርምስና እድሜ ማንነት በትክክል ስላልተቀፀ የተለያዩ ዝንባሌዎችን፣ ሀሳቦችን፣ እምነቶችን የሚሞከርበት ጊዜ ነው፡፡ በተያያዘም ብዙ ጊዜ ግልፅ ያልሆነውን ማንነት በተቃራኒ ጾታ ላይ በመሳል የአይን ፍቅር (ተነጋግረው ከማያውቁት/ቋት ሁሉ ሊሆን ይችላል፡፡) የሚይዝበት ጊዜ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የፍቅር ጥያቄ ለማቅረብም ሆነ የፍቅር ግንኙነት ለመጀመር ድፍረቱም ብስለቱም አይኖርም፡፡ ከዛ ይልቅ የተመሳሳይ ፆታ ጓደኝነት በተለይ በአስራዎቹ መጨረሻ በ'ግሩፕ' የሆነ ወዳጅነት የበለጠ ያጋጥማል፡፡
በጉርምስና ወቅት ተለዋዋጭ ስሜት፣ ከፍተኛ ድፍረት እና ቅጽበታዊ ውሳኔዎች የተለመዱ ቢሆኑም በእዚህ እድሜ ላይ የሚታዩትን ፀባዮች ሁሉ "ጉርምስና ነው፡፡" ብሎ ማለፍ ተገቢ አይደለም፡፡ በጣም ወጣ ያሉ ፀባዮች ሲታዩ ከአስተማሪያቸው፣ ከስነ ልቦና ባለሞያ እና በዋናነት ከነሱ ጋር መወያየት ጥሩ ነው፡፡ ቅፅበታዊ ውሳኔ ሊወስኑ እንደሚችሉ እያሰብን በ'ትልቅ ሰው' አክብሮት ማናገር ተመራጭ ነው፡፡
"ወላጆች ምናልባት ምክር ይሰጡ ይሆናል፡፡ ወይም ትክክለኛው ጎዳና ላይ ያስቀምጡ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ባህሪን የመገንባት የመጨረሻው ውሳኔ በግለሰቡ እጅ ነው፡፡"
አና ፍራንክ
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment