The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
አማኑኤል ሆስፒታል የሰው ድክመት፣ ውድቀት፣ ህመም ብቻ የሚሰማበት የሚመስላቸው ሰዎች አይጠፉም፡፡ ነገር ግን በየቀኑ የመነሳት፣ የጥንካሬ፣የፅናትና የፍቅር ውብ ታሪኮች ይስተናገዳሉ፡፡ ሁለቱ በዚህ ሳምንት ከገጠመኝ እነሆ፦
1) አማኑኤል የሴቶች ዋርድ የሀኪሞች ክፍል ተቀምጬ ካርድ ላይ እየፃፍኩ ነው፡፡ በሩ ገርበብ ብሏል፡፡ አንድ ታካሚ ከአልጋዋ ከነጋ አልተነሳችም፡፡ የደበራት ትመስላለች፡፡ ገርበብ ባለው በር ትታየኛለች፡፡ አንድ ወጣት ሴት ፍራፍሬ በፌስታል ይዛ ልትጠይቃት ትገባለች። አይኗ ብርት ብሎ ከአልጋዋ ወዲያው ተነሳች። ተቃቀፉ፡፡ በቀናት ውስጥ ያላየንባት ደስታ ውስጥ ሆና መጫወት ጀመሩ፡፡ ጠያቂዎን አውቃታለሁ፡፡ ከሳምንት በፊት እዚሁ ሆስፒታል እዚሁ ክፍል ተኝታ ነበር፡፡ ጓደኛዋን ልትጠይቅ መምጣቷ ነው፡፡ ተኝታ የምትታከመው ድንገት አቀረቀረች፡፡ አይኗን ሳታነሳ ጓደኛዋን "ግን የምንድን ይመስልሻል?" ብላ ጠየቀቻት፡፡ ጓደኛዋ እቅፍ አደረገቻት "እሱ የፈጣሪ ስራ ነው፡፡ እኛ ግን መድሀኒታችንን እንወስዳለን አለቻት፡፡"...
አንድ የኩላሊት ጠጠር ቀዶጥገና ሀኪም "ሀኪሙ ጠጠሩን ያወጣል፤ የሚያድነው ግን አምላክ ነው፡፡" ያለው ትውስ አለኝ፡፡
2) ታካሚ ወንድሙን ይዞ ኦፒዲ ይገባል፡፡ መልካቸው በጣም ይለያያል፡፡ "እባካችሁ ተኝቶ ይታከም?" አለን፡፡ "ያልተለመደ ፀባይ ሲታይበት አከራዮቻችን ቤት እንድንለቅ ጠየቁን፡፡ ለትንሽ ጊዜ ቢተኛ?" አለን፡፡ "ቤተሰቦቻችሁ የት ናቸው?" ብዬ ጠየቅኩት፡፡ መልሱ ያልጠበቅኩት ነበር፡፡ "ከተለያየ ቤተሰብ ነው የመጣነው ግን ወንድሜ ነው፡፡ በማደጎ አብረን ነው ያደግነው፡፡ እሱ ጎበዝ ተማሪ ነበር፡፡ እኔ ዱርዬ ነበርኩኝ፡፡ ማደጎውን ጥዬ ወጣሁ፡፡ ከዛ ጥሩ ያልሆነ ህይወት ነው ያሳለፍኩት፡፡ የተለያዩ ቦታዎች ዞሬ ስመለስ እሱ ኮሌጅ ተመርቋል ግን አእምሮውን አሞታል፡፡ ማንም አጠገቡ የለም፡፡ ስንገናኝ እኔ ያለፈው ህይወቴን ትቼ በእምንቴ ጠንክሬ ነበር፡፡ አሳከምኩትና ደህና ሆነ፡፡ አብረን መኖር ጀመርን፡፡ አሁን አመታት ሆኖናል፡፡ አንዳንዴ ያስቸግረኛል፡፡ ነገር ግን እኔ ራሴን ብዙ እንደተደረገለት ሰው ነው የምቆጥረው፡፡ ስለዚህ እሱን ማገዝ መቻሌን እንደ እድል ነው የማየው፡፡"....
በየሚዲያው በሚታየውና በሚሰማው እጅጉን ኮስምኖ የነበረው በሰብአዊነት ላይ የነበረኝ ግምት ሲለመልም ተሰማኝ።
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment