The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
ሲውዶሳዬሲስ ያለባቸው ሴቶች ያረገዙ ይመስላቸዋል፡፡ ከመምሰል ያልፍና የእርግዝና ምልክቶች ማሳየት ይጀምራሉ፡፡ የወር አበባ መቅረት፣ ማቅለሽለሽ፣ የጡቶች መጠን መጨመር፣ ሆድ መግፋት እና "የመውለጃ ጊዜያቸው" ሲደርስ የምጥ ስሜት ሁሉ ሊጀምራቸው ይችላል፡፡ እነዚህ ሁሉ ምልክቶች እያሉ ግን እርግዝና የለም፡፡
ከሲውዶሳዬሲስ ጋር ተያይዘው የሚመጡት አካላዊ ለውጦች ምክኒያቱ ስነ ልቦናዊ ነው፡፡ አብዛኛቹ ሲውዶሳዬሲስ የሚከሰትባቸው ሴቶች ማርገዝ ወይ በጣም ይፈራሉ ወይ በጣም ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ ላይ አካላዊ ለውጦችን በተዛባ መልኩ መተርጎም ሲጨመር የሰውነትን የሆርሞን ስርአት ልክ እንደ'ርግዝና እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
ሲውዶሳዬሲስ ልጅ መውለድን በሚያበረታቱ ማህበረሰቦች ውስጥ በሚገኙ መሀን ወይም ተደጋጋሚ ያልተፈለገ ውርጃ ያጋጠማቸው ሴቶች ላይ የመከሰት እድሉ ከፍ ያለ ሲሆን አስተማማኝ የእርግዝና ምርመራ ዘዴዎች ከተፈጠሩ በኃላ ሁኔታው በእጅጉ ቀንሷል፡፡ ሁኔታው ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀመሮ ተመዝግቦ የሚያውቅ ሲሆን በ16ኛው ክ.ዘ የእንግሊዝ ንግስት የነበረችው ሜሪ አንደኛ ሁለቴ ሲውዶሳዬሲስ አጋጥሟታል፡፡
ሲውዶሳዬሲስ እጅግ አልፎ አልፎ የሚከሰት ሁኔታ ይሁን እንጂ የአእምሯችን ሁኔታ አካላችን ላይ የሚኖረውን ተፅእኖ በማጠራጥር መልኩ ያሳያል፡፡
ያለ አእምሮ ጤና፤ ጤና የለም!
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment