The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
ራስን ማጥፋት በባህል የማንነጋገርበት ነገር ግን በኢትዮጲያ በአመት ከሰባት ሺህ ሰው በላይ ህይወቱን የሚያጣበት አሳዛኝ እውነታ ነው፡፡ ጓደኛ ወይም ዘመድ ራሱን ሲያጠፋ ሁልጊዜ ሙሉ ለሙሉ ሊመለስ የማይችል "ለምን?" የሚል ጥያቄ እና "እንዲህ አድርጌ በነበር!" የሚል ቁጭት ያስከትላል፡፡ አንድ ሰው ራሱን ለማጥፋት እንዲወስን የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች ቢኖሩም ዋነኛው ከባድ ዲፕረሽን ነው፡፡ ዲፕረሽን ከሚያስከትለውን የስነ ልቦና ስቃይ ለማምለጥ ብቸኛው አማራጭ ራስን ማጥፋት መስሎ ይታያል፡፡ ሰነ ልቦናዊ ምክኒያቶቹ በቀጣይ የሚቀርቡ ሲሆን ማህበረሰባዊ ምክኒያቶቹ እነሆ፦
- ባይተዋርነት፦ እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን የሚያጠፋት ከማህበረሰቡ ጋር ባለመዋሀድ ምክኒያት ነው፡፡ ደስታቸውን በይበልጥ ደግሞ ሀዘናቸውን የሚጋራቸው ባለመኖሩ ምክኒያት ባይተዋር ይሆናሉ፡፡
- መስእዋትነት፦ እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን የሚያጠፉት ከማህበረሰቡ ጋር በጣም በመዋሀዳቸው እነሱ ቢያልፉም ሞታቸው ለወገናቸው ክብር እና ጥቅም ስለሚያመጣ ነው፡፡ የጃፓን ካሚካዚ ጀት አብራሪዎች በሀገራችን ደግሞ አፄ ቴዎድሮስን ማንሳት ይቻላል፡፡ "ማረክን እንዳይሉ ሰው የለ በ'ጃቸው፣ ገደልን እንዳይሉ ሞተው አገኟቸው ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ ሀገራቸው፡፡" እንደተባለው፡፡
- ማህበራዊ ምስቅልቅል፦ ማህበራዊ አለመረጋጋት የሚፈጥሩ ሁኔታዎች እንደ ጦርነት፣ ስደት፣ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት የሰዎችን የእርስ በርስ ትስስር ስለሚያላሉት ራስን የማጥፋት እድልን ከፍ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ከላይ የተቀመጠው ክፍፍል የEmil Durkheim ራስን የማጥፋት ማህበራዊ እይታ ክፍፍል ላይ መሰረት ያደረገ ነው፡፡
ራስ ስለማጥፋት እያሰቡ ከሆነ ወይም የሚያውቁት ሰው እያሰበ ከሆነ ኢንቦክስ በማድረግ ወይም ፔጁ ላይ በተቀመጠው ቁጥር በመደወል ሞያዊ እገዛ ስለሚያገኙበት መንገድ ማናገር ይችላሉ፡፡
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment