The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
በጦርነት ወይም በግለሰብ ጥል ከሚሞቱት ሰዎች ራሳቸውን የሚያጠፉት በእጅጉን ይበልጣሉ፡፡ በየ አመቱ 800000 (በስህተት የተጨመረ ዜሮ የለውም) ሰዎች፡፡ ያ ማለት በሰው እጅ የምንሞት ከሆነ በራሳችን እጅ የመሆኑ እድል ከፍተኛ ነው፡፡
ሰዎች ራሳቸውን የሚያጠፉት በተለያየ ምክኒያት ሊሆን ይችላል፡፡ ጠቅለል ተደርገው በስነ ህይወታዊ፣ ስነ ልቦናዊ እና ማህበራዊ ሊመደቡ ይችላሉ፡፡
ኧርነስት ሄሚንግዌይ የስነ ጽሁፍ የኖብል ተሸላሚ የሆነ ተወደጅ ፀሀፊ ሲሆን በ1961 ሲሞት" ሽጉጡን ሲወለውል ባርቆበት ነው፡፡" ቢባልም ቆየቶ ባለቤቱ ራሱን እንዳጠፋ ተናግራለች፡፡ ሄሚንግዌይ አባቱ ራሱን ሲያጠፋ "እኔም በተመሳሳይ መንገድ ማለፌ አይቀርም፡፡" ብሎ ጽፎ ነበር፡፡
የሄሚንግዌይን የአእምሮ ጤንነት እና የቤተሰብ ታሪክ ካላወቅን በጥልቅ ባህር መዋኘት የሚወደው በቃላት ስዕል የሚስለው ባለ ብሩህ ጭንቅላቱ እና በአካል ጠንካራው ሰው ለምን ራሱን እንዳጠፋ እንቆቅልሽ ነው፡፡
የሄሚንግዌይ አባት፣ ወንድም፣ አያት እንዲሁም ልጁ ራሳቸውን ነው ያጠፉት፡፡ የቤተሰብ አባል ራሱን ሲያጠፉ የሚያስከትለው ስነ ልቦናዊ ጫና አንደተጠበቀ ሆኖ የሄሚንግዌይ ቤተሰብ ላይ የተደጋገመው ራስን ማጥፋት ተመራማሪዎች ስነ ህይወታዊ ምክኒያቶችን እንዲፈልጉ ያነሳሳ ነበር፡፡
ውጤቱ በቤተሰቡ ውስጥ ከነበረው የአእምሮ ህመም በተጨማሪ ራስን ከማጥፋት ጋር ተያያዥነት ያለው ዘረ-መል (suicidal gene) መኖሩን አመላክቷል፡፡ በተጨማሪም የአእምሮ "ኒውሮ ትራንስሚተር" ላይ የሚከሰቱ መዛባቶች ሚና ይኖራቸዋል፡፡
ራስን ማጥፋት ዘጠና ከመቶ ከአእምሮ ህመም ጋር የተያያዘ በመሆኑ በጊዜ አስፈላጊውን ህክምና በማድረግ መከላከል ይቻላል፡፡
ስለ ማህበራዊና ስነልቦናዊ መንስኤዎች በቀጣይ ይቀርባል፡፡
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment