The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
ፍቅር ይዞት ግጥም ጽፎ የሚያውቅ፣ ለናፍቆቱ ሙዚቃ ያዳመጠ ወይም ናፍቆቱን ሙዚቃ የቀሰቀሰበት የስነ ጥበብን የማከም አቅም የሚረዳው ነው፡፡ አርት ቴራፒ ስነ ጥበብን በመጠቀም ስነ ልቦናን ማከም ነው፡፡
አንዳንድ ስሜቶች በቃላት ለመግለፅ ያስቸግራሉ፡፡ በብሩሽና በቀለም ሲሆን መግለፅ የሚቀላቸው ሰዎች አሉ፡፡ የአእምሮ ህመም ያለባቸው ሰዎች በስነ ጥበብ ራሳቸውን ሲገልፁ የሚጋጩባቸውን ሀሳቦች እና ስሜቶች በተሻለ ሁኔታ ስለሚረዱ ስለራሳቸው ያላቸው ግንዛቤ ከፍ ይላል፡፡
የአርት ቴራፒ ተጨማሪ ጥቅሞች በራስ መተማመን ከፍ ማድረግ፣ የጭንቀትና የመከፋት ስሜትን መቀነስ፣ ያጋጠመን ነገር በተረጋጋ ሁኔታ ማጤን ..ወዘተ ናቸው፡፡ አንዳንድ ታካሚዎች አስደናቂ ስራዎችን ይሰራሉ፡፡ ነገር ግን አርት ቴራፒ ላይ ለመሳተፍ የሚያስፈልገው ችሎታ ሳይሆን ፍላጎት ብቻ ነው፡፡
ከላይ የተመለከተው በአማኑኤል ሆስፒታል አርት ቴራፒ ክፍል በታካሚ የተሰራ ነው፡፡
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment