The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
የአስተሳሰብ መዛባት ምክኒያታዊ ያልሆኑ፣ የተጋነኑ ወይም ከእውነታው ጋር የማይገናኙ ሀሳቦች የሚፈጥር ሲሆን ወደ አሉታዊ ስሜት አና ያልተገባ ፀባይ ያመራሉ፡፡ አስተሳሰብ፣ ስሜት አና ፀባይ ያላቸው ትስስር የ አስተሳሰብ መግራት ህክምና መሰረት ነው፡፡
ብዙ አይነት የአስተሳሰብ መዛባት አይነቶች ቢኖሩም የዛሬው ስለጥቁርና ነጭ አስተሳሰብ ነው፡፡ በጥቁር እና ነጭ አስተሳሰብ ነገሮችን፣ ሁኔታዎችንና ሰዎችን ሁለት ቦታ ከፍሎ በማየት በእያንዳንዱ ገጠመኝ ከማሰብና ከመገምገም ለመገላገል የሚደረግ (ውጤታማ ያልሆነ) ጥረት ሲሆን ምክኒያታዊ ስላልሆነ ስህተት እና አሉታዊ ስሜት ሊፈጥር ይችላል፡፡ የጥቁር እና ነጭ ምሳሌዎች፦
• ስኬት ወይም ውድቀት
• ወዳጅ ወይም ጠላት
• ክንፍ ያለው መልአክ ወይም ቀንድ ያለው ሴጣን
• በጣም ጥሩ ወይም በጣም መጥፎ
• ሁልጊዜ ወይም በጭራሽ
• እኛ ወይም እነሱ
ነገሮችን በጥቁር እና ነጭ መመደብ በተለይ ያልተለመዱ እና ጫና የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ውስጥ የሀሰት እርግጠኝነት ይሰጣል፡፡ ህይወት ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ ጽንፍ እና ፅነፍ ላይ የሚገኝ ሳይሆን የተለያዩ መጠን ያላቸው ነገርች ህብር ነው፡፡
ራሳችንን በጥቁር እና ነጭ ስናስብ ካገኘነው የሚከተሉት ጥያቄዎችን መጠየቅ ሚዛናዊ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ያግዛሉ፡፡
"ሌላ ምክኒያት ይኖረው ይሆን?"
"ሶስተኛ አማራጭ አለ?"
" ከድምዳሜዬ የሚቃረን ምሳሌ አለ?"...ወዘተ
ስለሌሎቹ የአስተሳሰብ መዛባቶች በሌላ ጊዜ ይቀርባል፡፡
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment