The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
ስለ ሳይኮአናላይሲስ ሲነሳ አቅጣጫዎች ሁሉ ወደ ሲግመን ፍሮይድ ይጠቁማሉ፡፡ እሱ ደግሞ የሳይኮአናላይሲስ መስራች ናት ብሎ ወደ አና ኦ ይጠቁማል፡፡ አና ኦ "የንግግር ፈውስ" የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የፈጠረች ናት፡፡ አና ታዋቂ የሆነችው በታካሚነት ነው፡፡
አና አባቷን እያስታመመች ትጨናነቅ ነበር፡፡ አባቷ ከሞተ በኃላ ብዙ አካላዊ ህመሞች ያስቸግሯት ነበር፡፡ ተደጋጋሚ ራስ ምታት፣ የቀኝ ሰውነት መዛል፣ ብዥ ማለት ...ወዘተ፡፡ የአካላዊ ህመሟ ምክኒያት ስነ ልቦናዊ በመሆኑ የሲግመን ፍሮይድ ጓደኛ የሆነ ሀኪም ለሁለት አመታት ያለ መድሀኒት ስለ አጋጠማት ነገር እንድትነግረው ያደርጋል፡፡ ቀስ በቀስ እየተሻላት ይመጣል፡፡ ስለህክምናው ስትናገር "የንግግር ፈውስ" ነው ትላለች፡፡
በጓደኛው ታካሚ ታሪክ የተነካው ፍሮይድ የመጀመሪያውን "የንግግር ህክምና" መንገድ ፈጠሮ ውጤታማነቱን አረጋግጠ፡፡ አሁን የንግግር ህክምና በአይነትም በውጤታማነትም እጅግ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ልክ የፍሮይድን አይነት የንግግር ህክምና የሚሰጡ አሉ፡፡ የሱን ዘዴዎች አሻሽለው የሚጠቀሙ አሉ፡፡ የሱን ዘዴ የማይቀበሉ እና አማራጭ መንገድ የቀየሱ አሉ፡፡ ነገር ግን ሁሉም በ የሆነ መንገድ ከሱ ጋር ይያዛሉ፡፡
አና ኦ ከህመሟ ከዳነች በኃላ በጀርመን ብዙ ማህበራዊ ስራዎችን የሰራች ሲሆን ላበረከተችው አስዋፅኦ እውቅና የጀርመን መንገስት በ1954 ምስሏን የያዘ ቴምብር አትሞ ነበር፡፡
የንግግር ህክምና ለእንዳንድ ህመሞች በብቸኝነት ለአንዳንድ ህመሞች ከመድሀኒት ጋር በተጓዳኝ የሚሰጥ ውጤታማ የህክምና አይነት ነው፡፡
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment