The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
ብዙ ሰው ህሊና የሌላቸው ሰዎች አሉ ብሎ ለመቀበል ያስቸግረዋል፡፡ በየጊዜያቱ የሚያደርሱት ሰቅጣጭ ድርጊት ግን ችላ እንዳይባሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ነገር ግን ህሊና የሌላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ስማቸውም ሳይኮፓት ይባላል፡፡ አደገኛ ስእብና ያላቸው ሰዎች ተብሎ ሊተረጎም ይቻላል፡፡
ሳይኮፓቶች ከምንም ነገር በላይ ስልጣንን ያስበልጣሉ፡፡ ከማህበረሰብም ሆነ ከግለሰብ ደህንነት በላይ፡፡ በተጨማሪም ለድርጊቶቻቸው ሀላፊነት አይወስዱም፡፡ የፀፀት ስሜትም አይሰማቸውም፡፡ ሌላኛው አደገኛ የሚያደርጋቸው 'ጭር ሲል' አይወዱም፡፡ ጭንቀት አያውቃቸውም፡፡ ግርግር እና ትርምስ ይወዳሉም ይፈጥራሉም፡፡ ሌሎች ሰዎች ሲጨነቁ ሲተራመሱ እነሱ ሴራ ያጠነጥናሉ፡፡
ለሳይኮፓቶች ሰዎች ሁሉ በሁለት የተከፈሉ ናቸው፡፡ ጠላት እና መጠቀሚያ፡፡ ለመጠቀሚያ ቢሆንላቸው ብቃትም ታማኝነትም ያላቸውን ሰዎች ይመርጣሉ፡፡ ካልሆነ ግን ብቃት ባይኖረውም ታማኝ የሆኑ ሰዎችን ያቀርባሉ፡፡ ያለ ብቃታቸው ቦታ የተሰጣቸው ሰዎች ታማኝነታቸው እንደሚጨምር ስለሚያውቁ፡፡
የማገናዘብ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሳይኮፓቶች በብዛት የሚገኙት እስር ቤት ሲሆን የማገናዘብ አቅማቸው ከፍ ያሉት ግን በሀይማኖት፣ በፖለቲካ እና በንግድ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ይደርሳሉ፡፡
ዶ/ር ሮበርት ሄር በአንድ ሳይኮፓት በደረሰባቸው ተደጋጋሚ ግፍ ምክኒያት ነው ስለ ሳይኮፓት ማጥናት የጀመሩት፡፡ "ሁኔታ አስገድዶት ነው እንጂ ሰው እንደዚህ ክፉ ሊሆን አይችልም!" ቢሉም ያለ ምንም ምክኒያት ጭምር ጉዳት ያደርስባቸዋል፡፡ ከዛ በኃላ ስለ ሳይኮፓቶች ብዙ ጥናት እና ምርምር ያደረጉ ሲሆን "ህሊና የሌላቸው" እና "ሱፍ የለበሱ እባቦች" የሚሉት መጻህፎቻቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ሳይኮፓቶች እንዴት እንደሚያስቡ፣ ስለሚያሳዩአቸው ፀባዮች እና ምን ማድረግ እንዳለብን በሌላ ጊዜ ይቀርባል፡፡
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment