The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
ከ1983 በፊት ኢትዮጲያ ውስጥ ሁለት የአእምሮ ህክምና ሆስፒታሎች ነበሩ፡፡ አስመራ የሚገኘው ሴንት ሜሪ እና አዲስ አበባ የሚገኘው አማኑኤል ሆስፒታል፡፡ ሁለት የተለያዩ ሀገራት ከሆኑ በኃላ በየሀገራቱ ብቸኛ የአእምሮ ሆስፒታሎች ሆነው ቀጥለዋል፡፡ ሴንት ሜሪ ስያሜውን ያገኘው( እንደ አማኑኤል )አጠገቡ ከሚገኘው የቅድስት ማርያም ካቴድራል ሲሆን ሲጀመር 120 አልጋዎች የነበሩት ሲሆን ከጊዜ በኃላ ወደ 160 ከፍ ብሏል፡፡
ሆስፒታሉ ለወንድ ታካሚዎች ሁለት ዋርዶች አሉት፡፡ አንዱ ለሚሊተሪ አንዱ ለሲቪል፡፡ የሴቶች ዋርድ አንድ ሲሆን ሲቪልም ሚሊተሪም በአንድነት የሚታከሙበት ነው፡፡ እንደ አማኑኤል የህፃናትና ታዳጊዎች አስተኝቶ ህክምና አይሰጥም፡፡
የአእምሮ ህክምና ከሀገሪቱ የጤና በጀት አምስት ከመቶውን ይይዛል፡፡ አብዛኛው በጀት የሚውለው በሴንቲ ሜሪ ሆስፒታል ነው፡፡ የመድሀኒት አቅርቦቱ ዝቅተኛ ቢሆንም ሁሉም የአእምሮ ህክምና መድሀኒቶች የሚሰጡት በነፃ ነው፡፡ በሀገሪቱ ያሉት ሳይካትሪስቶች ሁለት ሲሆኑ ለህዝብ ብዛቱ ያለው ምጣኔ ከኢትዮጲያ ጋር ተነጻጻሪ ነው፡፡ (ኤርትራ የህዝብ ቆጠራ አድርጋ ባታውቅም በሀገር ውስጥ የሚገኘው ህዝቧ ወደ 3.5 ሚሊዮን ይገመታል፡፡)
የኤርትራ መንግስት የአእምሮ ህክምና የሚያገኙ ሰዎችን መብት ለማስከበር ሁለት ህጎች አውጥቷል፡፡ የመጀመሪያው ሁሉም መስሪያ ቤቶች ካላቸው ሰራተኛ አምስት ከመቶ አካል ጉዳተኛ ሰዎችን እንዲያካትቱ የሚያስገድድ ሲሆን ሁለተኛው በአእምሮ ህመም ምክኒያት አድልዖ (ዝቅተኛ ክፍያ፣ ከስራ መቀነስ) እንዳይደርስ የሚከላከል ነው፡፡
ምንጭ የአለም የጤና ድርጅት በኤርትራ አእምሮ ጤና ላይ በ2006 ዓም ያቀረበው ሪፖርት
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment