The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ማህበራዊ መገለል በጤንነት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት አስራአምስት ሲጋራ በቀን በማጨስ ከሚመጣው ጋር ተነፃፃሪ ነው፡፡እንግሊዝ የመጀመሪያዋን የብቸኝነት ሚኒስትር አድርጋ ትሬሲ ክራውችን ስትሾም የብቸኝነት ጉዳይን በሚኒስተር ደረጃ ስታቋቁም በዚህ ምክኒያት ነው፡፡
ላይ ላዩን ሲታይ ብቸኝነት በዘመናዊነት ምክኒያት የመጣ የምዕራባውያን ማህበራዊ ችግር ሊመስል ይችላል፡፡ ያለን ማህበራዊ ትስስር ጥብቅ መሆኑ ለአእምሮ ጤንነት የሚረዳ ነው፡፡ የአእምሮ ህመምን በሚመለከት ግን ሁሉም በተናጥል የሚጋፈጠው ነገር ነው፡፡ በእውቀቱ ስዩም በጥሩ መልኩ ገልጾታል፡፡
"የጋራችን ዓለም የጋራችን ሰማይ፣
የብቻችን ህመም የብቻችን ሰቃይ፡፡"
ብቻነትን አና ብቸኝነትን መለያየት ያስፈልጋል፡፡ ብቸኝነት በሰው ተከበንም ሊፈጠር የሚችል ክስተት ነው፡፡ስለብቸኝነት በሌላ ጊዜ ይቀርባል፡፡ የዚህ ፅሁፍ አላማ ሀገራት ለአእምሮ ጤና የሚሰጡትን ትኩረት አና አኛስ የት ነን? የሚለውን ለመጠየቅ ነው፡፡
ያለ አእምሮ ጤና ጤና የለም፡፡
መልካም ጊዜ!
Comments
Post a Comment