Skip to main content

Posts

Showing posts from 2018

Featured Post

አስፐርገር ሲንድረም (Asperger syndrome)

The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር  ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው

አስፐርገር ሲንድረም (Asperger syndrome)

The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር  ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው

ስለማሰብ ማሰብ

ዘመናዊነት፣ ትምህርት፣ፍትህ ከአዲስ የማሰቢያ መንገድ ውጭ ምንድናቸው? የሰው ልጆች እጅግ አስደናቂ ችሎታችን ማሰብ ከመቻላችን በላይ ስለማሰብ ማሰብ መቻላችን ነው፡፡ ስለማሰብ ማሰብ የምናስብበትን መንገድ ለማሻሻል ከማስቻሉም በላይ ሌሎች ሰዎችን በተሻለ ለመረዳት ያስችላል፡፡ ስለምናስበበት መንገድ አብዝተን ባሰብንና ስለሀሳቦቻችን የተረዳነውን ተግባር ላይ ስናውል የበለጠ ደስተኛ የበለጠ ውጤታማ እንሆናለን፡፡   ሀሳባችን እውነታውን ሊወክልም ላይወክልም ይችላል፡፡ "እኔ ያሰብኩት ነው እውነታው!" ብሎ ክችች ማለት ስለማሰብ እያሰብን እንዳልሆነ ያሳያል፡፡ በእንግሊዘኛው Psychic equivalence ይባላል፡፡ምናባችንን ወደ እውነታው ከማምጣት እውነታውን ወደ ምናባችን ለማምጣት እንደመጎተት ነው፡፡ ሀሳባችን ማለት ሙሉ ለሙሉ እኛን አይወክልም፡፡ ሀሳባችን የኛ እንጂ እኛ አይደለም፡፡ ስለማሰብ ማሰብ የአስተሳሰብ ስህተቶቻችንን መለየት፣ ጠቃሚ የሆኑትን ማጠናከር እና ሂደቱን በተከታታይ ማስተዋል ነው፡፡ የንግግር ህክምና(Psychotherapy) በቀላሉ ሲገለፅ ሰዎች ከሀሳባቸው ትንሽ ወደ ወደ ኃላ ብለው ሀሳባቸውን በራሳቸው መመርመርና መለወጥ እንዲችሉ ማገዝ ነው እንጂ ብዙዎች እንደሚመስላቸው ሰዎችን መምከር አይደለም፡፡   አስተሳሰባችንን ስንለውጥ የየራሳችን ትንሿን አለማችንን መለወጥ እንችላለን፡፡   መልካም ጊዜ!

ሁለት ውብ ታሪኮች ከአማኑኤል ሆስፒታል

አማኑኤል ሆስፒታል የሰው ድክመት፣ ውድቀት፣ ህመም ብቻ የሚሰማበት የሚመስላቸው ሰዎች አይጠፉም፡፡ ነገር ግን በየቀኑ የመነሳት፣ የጥንካሬ፣የፅናትና የፍቅር ውብ ታሪኮች ይስተናገዳሉ፡፡ ሁለቱ በዚህ ሳምንት ከገጠመኝ እነሆ፦   1) አማኑኤል የሴቶች ዋርድ የሀኪሞች ክፍል ተቀምጬ ካርድ ላይ እየፃፍኩ ነው፡፡ በሩ ገርበብ ብሏል፡፡ አንድ ታካሚ ከአልጋዋ ከነጋ አልተነሳችም፡፡ የደበራት ትመስላለች፡፡ ገርበብ ባለው በር ትታየኛለች፡፡ አንድ ወጣት ሴት ፍራፍሬ በፌስታል ይዛ ልትጠይቃት ትገባለች። አይኗ ብርት ብሎ ከአልጋዋ ወዲያው ተነሳች። ተቃቀፉ፡፡ በቀናት ውስጥ ያላየንባት ደስታ ውስጥ ሆና መጫወት ጀመሩ፡፡ ጠያቂዎን አውቃታለሁ፡፡ ከሳምንት በፊት እዚሁ ሆስፒታል እዚሁ ክፍል ተኝታ ነበር፡፡ ጓደኛዋን ልትጠይቅ መምጣቷ ነው፡፡ ተኝታ የምትታከመው ድንገት አቀረቀረች፡፡ አይኗን ሳታነሳ ጓደኛዋን "ግን የምንድን ይመስልሻል?" ብላ ጠየቀቻት፡፡ ጓደኛዋ እቅፍ አደረገቻት "እሱ የፈጣሪ ስራ ነው፡፡ እኛ ግን መድሀኒታችንን እንወስዳለን አለቻት፡፡"... አንድ የኩላሊት ጠጠር ቀዶጥገና ሀኪም "ሀኪሙ ጠጠሩን ያወጣል፤ የሚያድነው ግን አምላክ ነው፡፡" ያለው ትውስ አለኝ፡፡   2) ታካሚ ወንድሙን ይዞ ኦፒዲ ይገባል፡፡ መልካቸው በጣም ይለያያል፡፡ "እባካችሁ ተኝቶ ይታከም?" አለን፡፡ "ያልተለመደ ፀባይ ሲታይበት አከራዮቻችን ቤት እንድንለቅ ጠየቁን፡፡ ለትንሽ ጊዜ ቢተኛ?" አለን፡፡ "ቤተሰቦቻችሁ የት ናቸው?" ብዬ ጠየቅኩት፡፡ መልሱ ያልጠበቅኩት ነበር፡፡ "ከተለያየ ቤተሰብ ነው የመጣነው ግን ወንድሜ ነው፡፡ በማደጎ አብረን ነው ያደግ...

ማዶና ፑታና ኮምፕሌክስ

ማዶና ፑታና ኮምሌክስ ሁኔታዊ (Situaional) ስንፈተ ወሲብ ነው፡፡ ከሚወዷት ፍቅረኛ ወይም ሚስት ጋር ሴክስ ለማድረግ አለመቻልና በተቃራኒው ከሴተኛ አዳሪ ጋር ምንም ስንፈት አለመኖር ሲሆን በተለይ ሚስቶች ልጅ ከወለዱ በኀላ የሚፈጠር ነው፡፡ ይህ ስነ ልቦናዊ ኮምፕሌክስ ያለባቸው ሰዎች የፍቅር ስሜት ላላቸው ሰው የሴክስ ፍላጎት አይኖራቸውም፡፡ የሴክስ ፍላጎት ላላቸው ሰው ደግሞ የፍቅር ስሜት የላቸውም፡፡ሴክስና ፍቅር ሳይዋሀዱ እንደ ዘይት እና ውሀ ሆነው አእምሮ ውስጥ ሲቀመጡ የሚፈጠር ነው።   እነዚህ ሰዎች ሴቶችን ሁሉ በሁለት ይከፍላሉ፡፡ ንፅህት እና ባለጌ፡፡ የሚሰማቸውም ፍቅር በሁለት የተከፈለ ነው፡፡ ንፁህ ፍቅርና የብልግና፡፡ ሚስቶቻቸው ልጅ ከወለዱ በኃላ እንደ ሚስት ሳይሆን እንደ እናት ማየት ይጀምራሉ፡፡ ሴክስ ፎሮይድ እንደሚለው ሁሉንም ፀባይ የሚወስን አይሁን እንጂ ከአካላዊ ድርጊቱ ግን የዘለለ ስነ ልቦናዊ እና መንፈሳዊ ትርጉም ያለው እንደሆነ እርግጥ ነው፡፡ ሴክስ 'ባለጌ ነገር' እየተባለ በሚነገርበት ሁኔታ ውስጥ ማደግ የሚያስከትለው ተፅዕኖ ምን ይሆን? ሴክስ አብዛኛው ነገሩ የሚካሄደው በእግሮች መሀል ሳይሆን በጆሮዎች መሀል ነው፡፡ መልካም ጊዜ!

ማስቲሽ ማሽተት፤ቤንዚን መሳብ

ማስቲሽ ወይም ቤንዚን ከሌሎቹ ሱስ አምጪ ነገሮች በተለየ በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉ፣ ውድ ያልሆኑና ህገ ወጥ ያልሆኑ ናቸው። እነዚህ ሶስት ምክኒያቶች እድሜያቸው ለጋ በሆኑና ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ በሚገኙ ልጆች እንዲዘወተሩ አድርጓቸዋል። ለዚህ ድርጊት የሚውሉት የተለያዩ ነዳጆች፣ ማስቲሽ፣ የሚነፉ ቀለሞች ፣ ጥፍር ቀለም ማስለቀቂያዎች እና የተለያዩ የቀለም ማቅጠኛዎች...ወዘተ ናቸው፡፡ የሚሳቡት ኬሚካሎች አንዳንዶች ላይ 'ለቀቅ' የማለት እና የነውጠኝነት ስሜት፣ ሌሎች ላይ ድክምክም ማለት ይፍጠሩ እንጂ በተደጋጋሚ እንዲወሰዱ የሚያደርጋቸው ለተወሰነ ጊዜ የሚቆየው 'የመንሳፈፍ አይነት ደስታ' ነው። ከፍ ባለ መጠን ከተወሰደ የፍርሀት ስሜት፣ የሌሉ ድምጾች መስማት እንዲሁም ለረጅም ጊዜ ሲወሰድ የአእምሮ እድገትና በተለይ የማስታወስ ችሎታ ላይ ጉዳት ያደርሳል፡፡ በሌሎች ሀገራት የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ይህ ችግር በታዳጊዎች ላይ በይበልጥ እንደሚታይና ለመከላከል የሚረዱ ስርአቶች እንዳሏቸው ነው፡፡ በሀገራችን የተሰራ ጥናት አላገኘሁም፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩ ስለመኖሩ ቁጥሮች ባይገኙም የአዲስአበባ ዋና ዋና ጎዳናዎች ግን ይመሰክራሉ፡፡ ትኩረት እንደሚፈልግ አያጠያይቅም! መልካም ጊዜ!

ፈገግተኛ ዲፕረሽን (Smiling depression)

ፈገግተኛ ዲፕረሽን ከተለመደው ዲፕረሽን ወጣ ያለ ሲሆን እነዚህ ሰዎች የሚሰማቸውን መከፋት፣ ተስፋ ማጣት...ወዘተ በውስጣቸው ይዘው በአብዛኛው ፈገግታ የሚታይባቸውና በሌሎች ሰዎች እንደ ደስተኛ የሚታዩ ናቸው፡፡ በአብዛኛው ትዳር/የፍቅር ጓደኛ፣ ስራ አላቸው፡፡ በስራቸው ስኬታማ፣ በማህበራዊ ኑሯቸው ጥሩ ይሁኑ እንጂ ለብቻቸው ሲሆኑ ተስፋ መቁረጥ፣ መሰላቸት፣ የእንቅልፍ ችግር ያጋጥማቸዋል፡፡   ዲፕረሽን ሁሉም ሰው ላይ በተመሳሳይ የሚገለፅ ህመም አይደለም፡፡ ስራውን እየሰራ ስለሆነ ግለሰቡ ራሱ ዲፕረሽን እንዳለበት ላይረዳ ይችላል፡፡ፈገግተኛ ዲፕረሽን ከዲፕረሽን የባሰ የሚያደርገው ዲፕረሽን ያላቸው ሰዎች ራስን የማጥፋት ሀሳብ ቢኖራቸውም ለመሞከር አቅም ስለማይኖራቸው ራስን የማጥፋት እድላቸው(በንፅፅር)ዝቅ ያለ ነው፡፡ በእምነት ጠንካራ መሆንና የልጆች መኖር ራስን ከማጥፋት በከፍተኛ ደረጃ የሚከላከሉ ይሁኑ እንጂ መቶ ከመቶ ያስቀሩታል ማለት አይደለም፡፡   አንዳንድ ፈገግተኛ ዲፕረሽን ያለባቸው ሰዎች ዲፕረሽንን እንደ ድክመት ስለሚያዩት ሞያዊ እርዳታ ለማግኘት ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡ በአጠቃላይ መከፋትን በተመለከተ በጣም አስፈላጊ ነገር ስሜትን መናገር መቻል ነው፦ለጓደኛ፣ ለቤተሰብ እንዲሁም ሞያዊ እገዛ የሚያስፈልግ ከሆነ ከስነ ልቦና ባለሞያ ወይም ከአእምሮ ሀኪም ጋር መነጋገር ጥሩ ነው።   ፈገግተኛ ዲፕረሽን ላይ በብዛት ከሚከሰቱ ስሜቶች አንዱ ብቸኝነት ሲሆን ብቻዎን እንዳልሆኑና ዲፕረሽን ውጤታማ በሆነ መልኩ ሊታከም የሚችል ህመም መሆኑን ማስታወስ ጥሩ ነው፡፡ መልካም ጊዜ!

የእርጅና ስነ ልቦና

እርጅና ሲመጣ የሰዎች ትኩረት ከገንዘብ ወደ ጤንነት ይዛወራል፡፡ በጉልምስና ወቅት ብዙ ሰዎችን የሚያሳስባቸው ከሰው ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት እና ስራ ሲሆን በእርጅና እድሜ የሚከሰተውን አካላዊ ለውጦች ወይም ህመሞችን ተከትሎ የሚያሳስባቸው በይበልጥ አካላዊ ሁኔታ ነው፡፡    በእርጅና እድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ሰባት ተጨማሪ አመታት የሚኖሩ ሲሆን አንድ አያት ብቻ ካለን ብዙ ጊዜ ሴት አያት ነው የሚኖረን።   በእርጅና እድሜ የሚጠበቁ ነገሮች፦  ህይወትን ዞር ብሎ መቃኘት ከቁሳዊ ነገሮች ጋር ያለ ቁርኝት መቀነስ የትዳር አጋር/ ጓደኞችን ማጣት የሚፈጥረውን ሀዘን መቋቋም ከጡረታ ጋር የተያያዙ ለውጦችን መቀበል ከልጅ ልጅ ጋር የሚኖር ግንኙነት...ወዘተ  እንደ ኤሪክሰን በእርጅና እድሜ ላይ ሰዎች ያለፉበትን ይቃኙና ባሳለፉት ህይወት ደስተኛ ከሆኑ እርካታና ሰላም ይሰማቸዋል፡፡ በተጨማሪም ሞትን በፀጋ ለመቀበል ዝግጁ ናቸው፡፡ "ሞት ሆይ መውጊያህ የታለ የሚሉ ይመስላል፡፡"በአንፃሩ ህይወት አጭር እንደሆነ፣ በህይወታቸው ትክክለኛ ውሳኔ እንዳልወሰኑና ለማስተካከል ጊዜ እንደሌላቸው የሚያስቡ ከሆነ ውጤቱ መበሳጨት እና ንጭንጭ ይሆናል፡፡   "አርባ አመት ለወጣቶች የእርጅና እድሜ ሲሆን ለሽማግሌዎች ሀምሳ አመት የወጣትነት እድሜ ነው፡፡" ቪክቶር ሁጎ መልካም ጊዜ!

የትም ቦታ ብንሄድ እዛም ያለነው እኛው ነን!

ይህ በጆን ካባት-ዚን የተፃፈው ምርጥ መፅሀፍ ርዕስ ነው፡፡ ርዕሱ እንደሚገልፀው የትም ቦታ ብንሄድ ራሳችንን ይዘን ነው፡፡ አስፈላጊነቱ "ሌላ ቦታ በሆንኩኝ!" እያሉ መመኘትን እንድናቆም ነው፡፡ እረፍት ላይ ብሆን፣ ከሌላ ፍቅረኛ /የትዳር አጋር ጋር ብሆን፣ ሌላ ትምህርት ተምሬ ቢሆን፣ ሌላ ስራ ቢኖረኝ፣ ሌላ ቤት ውስጥ ብኖር፣ ሌላ ሁኔታ ውስጥ ብሆን...ደስተኛ እሆን ነበር ብለን እናስባለን፡፡ ደስተኛ አንሆንም!   በእውነታው ጎጂ የሆነ የአስተሳሰብ ልማድ ካለን ማለትም በቀላሉ የምንናደድ ከሆነ፣ ትንንሽ ነገሮች የሚያበሳጩን ከሆነ፣ ነገሮች የተለዩ ቢሆኑ ብለን የምንመኝ ከሆነ የትም ብንሄድ እነዚህ ልማዶች ይከተሉናል፡፡ በተቃራኒውም ደግሞ እውነት ነው፡፡ በአብዛኛው በትንሹ የማይናደድ ደስተኛ ሰው ከሆንን ቦታ ብንለውጥም ከሌላ ሰው ጋር ብናሳልፍም ሳንጨነቅ ጥሩ ጊዜ ይኖረናል፡፡ አንድ ጊዜ አንድ ሰው "እናንተ አካባቢ ያሉ ሰዎች ምን አይነት ናቸው?" ብሎ ጠየቀኝ፡፡ እኔም መልሼ "መጀመሪያ እናንተ አካባቢ ያሉት ሰዎች ምን አይነት ናቸው?" ብዬ ጠየቅሁት፡፡ "ስግብግብና ራስ ወዳድ ናቸው፡፡" ብሎ መለሰልኝ፡፡ "እኛ አካባቢ ያሉትንም ሰዎች እንደዚያው የምታገኛቸው ይመስለኛል፡፡" አልኩት፡፡   ህይወት እንደመኪና ከውስጥ ወደ ውጭ እንደሚሽከረከር ስንገነዘብ አስገራሚ ነገሮች መፈጠር ይጀምራሉ፡፡ ከውጭ ወደ ውስጥ አይሆንም! ሌላ ቦታ፣ ሌላ ሁኔታ ቢሆን የሚለውን ምኞት ትተን አሁን ያለንበትን ቦታ የተሻለ ማድረግ ላይ ስናተኩር አሁን እዚሁ ደስተኛ መሆን እንጀምራለን፡፡ ከዛ ቦታ ብንለውጥም፣ አዲስ ነገር ብንሞክርም፣ አዲስ ሰዎች ስናገኝም ውስጣዊ እር...

ስብሃት ገብረእግዚያብሄር የአእምሮ ህመምን እንደፃፈው-1

በሰባተኛው መልአክ ላይ የተተረከው አየለ ነብር ስኪዞፍሬኒያ የሚባል የአእምሮ ህመም እንዳለበት ማወቅ ይቻላል፡፡ የአእምሮ ህመሙን አስመልክቶ የተፃፈው ሳይንሳዊ ትክክለኛነቱ (Scientific accuracy) ከፍተኛ ከመሆኑ ባሻገር ስለ አእምሮ ህመም ያለንን ማህበረሰባዊ እይታ በደንብ የሚያሳይ ነው፡፡ አየለ ከሰዎች ስለ አእምሮ ህመሙ የተባለውን ሲገልፅ ገፅ 76"...ደግሞ በመታመሜ ሀበሾች በጣም ነው ያፈሩብኝ፣ በጣም ነው የናቁኝ፣ አንተ ባትኖር የሚያሳፍር ይመስለኝ ነበር፡፡ በህመም ላይ እፍረት። ይታይሀል? አንተና ያሲን ብቻ ናችሁ ሁኔታዬን አስጨናቂ ሸክም ነው እንጂ አሣፋሪ ውድቀት አይደለም ያላችሁኝ። ይህ አስተያየታችሁ ብዙ አግዞኛል። ብዙ" በተጨማሪ ስለ መገለልና መድልዖ ገፅ 68 "...ያሲን ሀበሾችን ታዘባቸው። ሁልጊዜ አንድ ላይ ስለሚያያቸው የሚዋደዱ፣ የሚተዛዘኑ ይመስለው ነበር። አሁን ግን አንድ ላይ የሚታጎሩት ለመለያየትና በየፊናቸው ለመሄድ ባለመድፈራቸው ብቻ መሆኑ እየገባው ሄደ። ፈተና ደርሶብናል እያሉ አየለን ለኛ ጥለውልን ይሄዳሉ፣ ግን ቢያንስ በቀን ሶስት ሰአት ካፌ ውስጥ እያወሩ ወይም ካርታ እየተጫወቱ ማሳለፋቸው አልቀረም፡፡ ታዲያ እኔንና ያሲንን ሲያገኙን ስለ አየለ "ምክር ለበስ ቁም ነገር" ያካፍሉናል፡፡ "ሀኪም ቤት መሄድ አልፈልግም አለ፣ ወይ ጉድ ምን ይሻላል? ምናልባት አንዳንዴ ወደ ገጠር ሽርሽር ብትወስዱት አንጎሉን ሳያድስለት ይቀራል?...ልጁ እንደመክሳት ሳይል አልቀረም። የአሳማ ስጋና ፍራፍሬ ቢበላ ነፍሱን መለስ ያደርግለት ይሆናል እኮ። ሙዚቃ! ለተጨነቀች ነብስ ከሙዚቃ የበለጠ የሰላም መልእክተኛ ከየት ተገኝቶ! ወዘተ። ነገር ግን ...

ምላሴ/ አፌ ላይ አለ

ባለፈው የሄድንበት ቦታ የት ነበር? ...እ .እ ምላሴ ላይ አለ፡፡ ከስሙ በስተቀር ሌሎች ዝርዝሮችን ልናስታውስ እንችላለን፡፡ ይህ በሳምንት አንዴ አብዛኛው ሰው ላይ የሚያጋጥም ነገር ነው፡፡ በስነ ልቦና የሚታወቅ ክስተት ሲሆን ሌቶሎጂካ (lethologica) ይባላል፡፡ እድሜ ሲጨምር እየተደጋገመ ይመጣል፡፡ በጊዜያዊነት አንድን ነገር መርሳታችንን ተከትሎ ለጥቂት ደቂቃዎችም ቢሆን በቃላት ለመግለፅ የሚያስቸግር የጭንቀት ስሜት ይፈጥራል፡፡ "ምላሴ/አፌ ላይ ነው።" ግን ምንድነው? ሌቶሎጃካ አለማቀፋዊና በሁሉም ቋንቋዎች የሚከሰት መረጃን ሸራርፎ ማስታወስ ነው፡፡ ቋንቋ ምንም ያህል የተወሳሰበ ሂደት ቢሆንም አእምሯችን ሀሳቦችን ወደ ቃላት በከፍተኛ ቅልጥፍና ስለሚለውጣቸው እንደስራ አንወስደውም(በብዛት)።ቃሉ ምላሳችን ላይ ሲሆን እንደምናውቀው እናውቃለን፣ የሰማንበት ቦታ ወይም የመጀመሪያዐው ፊደል ትዝ ይለናል፡፡ ግን ቃሉ የለም፡፡ ምክኒያቱ አእምሯችን የአንድን ቃል ድምፀቱን አንድ ቦታ፣ ፊደሉን ሌላ ቦታ፣ የሚወክለውን ሀሳብ ሌላ ቦታ ሴቭ ስለሚያደርግ ነው፡፡በድንገት ይመጣልንንና ወይም ሰው ሲያስታውሰን 'እፎይ' እንላለን፡፡   ይህ ክስተት በሳይንሳዊ ስያሜው ሌቶሎጂካ ቢባልም በአማርኛ "ምላሴ/አፌ ላይ ነው፡፡" በትግርኛ "ኣብዛ ኣፈይ እያ ዘላ" በኦሮምኛ "arraba koo irra jira" ይባላል፡፡ በፈረንሳይኛም በኮርያኛም በሁሉም ቋንቋ ተመሳሳይ ምላሴ ወይም አፌ ላይ ነው የሚል ትርጉም ነው ያለው፡፡   አስተማሪ፡ H2SO4 የምን ፎርሙላ ነው? ተማሪ፡ ምላሴ ላይ አለ፡፡ አስተማሪ፡ ሰልፈሪክ አሲድ ነው ያቃጥልኸል ትፋው፡፡ መ...

የጉርምስና ስነልቦና

ጎረምሶች አካላቸው ከፍ ያለ ህፃናት ናቸው? ወይስ አእምሯቸው ያልበሰለ 'ትልቅ ሰዎች'? ጉርምስና የሚጀምረው በአካላዊ ለውጦች ሲሆን ስነ ልቦናዊ ለውጦቹ በኃላ የሚመጡ ናቸው፡፡ አካላዊ ለውጦቹ ስለ ራሳቸው አብዝተው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል፡፡ አንዳንዶች ላይ ብጉር፣ የድምፅ መቀየር እና ሌሎች አካላዊ ለውጦች የተዘባ አካላዊ እይታ በዘለቄታው እንዲኖራቸው ሊያደርግ ይችላል፡፡ በተጨማሪም አብዛኛው ሶሻል ፎቢያ የሚጀምረው በአስራዎቹ እድሜ ውስጥ ነው፡፡ ጉርምስና የቤተሰብ ልጅ ከመሆን በራስ ሰው ወደ መሆን የሚደረግ ሽግግር በመሆኑ ብዙ ጊዜ ከቤተሰብ ጋር አለመግባባት ይስተዋልበታል፡፡ በጉርምስና እድሜ ላይ ለሚገኙ ታዳጊዎች በአለም ላይ እጅግ አስፈላጊው ነገር በእኩዮቻቸው /ጓደኞቻቸው እይታ ተፈላጊ ወይም "cool" መሆን ነው፡፡ አንዳንዶቹ በቤተሰባቸው ጣልቃ ገብነት እፍረት ይሰማቸዋል፡፡ ብዙ በዚህ እድሜ ላይ የሚገኙ ታዳጊዎች ልዩ እንደሆኑና ማንም እንደማይረዳቸው ያስባሉ፡፡ በጉርምስና እድሜ ማንነት በትክክል ስላልተቀፀ የተለያዩ ዝንባሌዎችን፣ ሀሳቦችን፣ እምነቶችን የሚሞከርበት ጊዜ ነው፡፡ በተያያዘም ብዙ ጊዜ ግልፅ ያልሆነውን ማንነት በተቃራኒ ጾታ ላይ በመሳል የአይን ፍቅር (ተነጋግረው ከማያውቁት/ቋት ሁሉ ሊሆን ይችላል፡፡) የሚይዝበት ጊዜ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የፍቅር ጥያቄ ለማቅረብም ሆነ የፍቅር ግንኙነት ለመጀመር ድፍረቱም ብስለቱም አይኖርም፡፡ ከዛ ይልቅ የተመሳሳይ ፆታ ጓደኝነት በተለይ በአስራዎቹ መጨረሻ በ'ግሩፕ' የሆነ ወዳጅነት የበለጠ ያጋጥማል፡፡ በጉርምስና ወቅት ተለዋዋጭ ስሜት፣ ከፍተኛ ድፍረት እና ቅጽበታዊ ውሳኔዎች የተለመዱ ቢሆኑም በእዚህ እድሜ ላይ የሚታዩት...

የጆሀሪ መስኮቶች: የማንነታችን አራቱ ክፍሎች

  የጆሀሪ መስኮቶች ከሰው ጋር እንዲሁም ከራሳችን ጋር ያለንን ግንኙነት በተሻለ ለመረደት የሚያግዝ ንድፍ ነው፡፡ ጆሀሪ ስያሜውን ያገኘው ንድፉን በጋራ ከፈጠሩት የስነ ልቦና ባለሞያዎቹ ጆሴፍ ለፍት እና ሀሪንግተን ኢንግሀምን ስም በማቀናጀት ነው፡፡ ማንነታችን በአራት ሊከፈል ይችላል፦ ግልፅ፣ ድብቅ፣ የተሰወረ እና ጨለማ፡፡ ግልፁ ማንነት፦ ይሄኛው ስለራሳችን እኛም ሌላውም ሰው የሚያውቀው ሲሆን ድርጊቶችን፣ እውቀትን፣ ክህሎትን ያጠቃልላል፡፡ ስለዚህኛው ማንነታችን ከሰዎች ጋር ለመነጋገር ችግር የለብንም በተጨማሪም ሰዎች ስለዚህ የማንነታችን ክፍል በሚሰጡት አስተያየት በብዛት እንስማማለን፡፡   ድብቁ ማንነት፦ ይህ ማንነት ራሳችን የምናውቀው ሲሆን ከሌሎች የተደበቀ ነው፡፡ በዚህ መስኮት ውስጥ ያሉ ማንነቶቻችንን ስለምናፍርባቸው ወይም የግል ህይወታችን ስለሆኑ ተጋላጭ እንዳንሆን ከሌሎች እንደብቃቸዋለን፡፡ በተመሳሳይ በትህትና ምክኒያት ሰዎች እንዲያውቁ የማንፈልጋቸው ችሎታዎቻችን እውቀታችንንም ያካትታል፡፡   የተሰወረ ማንነት፦ ይሄኛው ሌሎች ሰዎች የሚያዩት ከኛ ግን የተሰወረው ማንነት ነው፡፡ ምክኒያታዊ እንደሆንን እናስብ ይሆናል ሰዎች ግን ግትር እንደሆንን ነው የሚያውቁት፡፡ ወይም ራሳችንን 'ምንም እንደማያውቅ 'ልናስብ እንችላለን ሰዎች ግን በጣም ብልህና አስተዋይ እንደሆንን ሊረዱ ይችላሉ፡፡ በዚህ መስኮት ውስጥ ነው ሰዎች ቃላችን እና ድርጊታችን እንደሚለያይ የሚያስተውሉት፡፡   ጨለማ (የማይታወቀው) ማንነት፦ ይህ ማንነት በራሳችንም ሆነ በሌሎች የማይታወቅ ክፍል ነው፡፡ ጥሩም ጥሩ ያልሆኑ ሀሳቦች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ በአጠቃላይ የ ጆሀሪ መስኮቶቸ ራሳችንን ለመረዳት...

ፓኒክ ዲስኦርደር- "ፍርሀትን መፍራት"

ፓኒክ በድንገት የሚመጣ ከፍተኛ ፍርሀት ሲሆን አእምሯዊም አካላዊም ምልክቶች አሉት፡፡ ትንፋሽ ማጠር፣ ልብ ቶሎ ቶሎ መምታት፣ ማላብ፣ መደንዘዝ፣ ማቅለሽለሽ "ልሞት ነው?" "አእምሮዬን ልስት ነው?" የሚሉ ሀሳቦች፡፡ ፓኒክ ግፋ ቢል አስር አስራአምስት ደቂቃየሚቆይ ይሁን እንጂ ፓኒክ ያጋጠማቸው ሰዎች ያላሰቡት ቦታ ወይም ሁኔታ ውስጥ ድጋሚ እንዳያግጥማቸው መፍራት እና መጨነቅ ይጀምራሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከቤት ውጭ ፓኒክ እንዳያግጥማቸው በመፍራት ከቤት የማይወጡ ሰዎች አሉ፡፡ ለዚህ ነው ፓኒክ ዲስኦርደር "የፍርሀት ፍርሀት" የሚባለው፡፡   ፓኒክ ዲስኦርደር ከመቶ ሰው ከአንድ እስከ አራት ሰው ላይ ሊከሰት የሚችል ሲሆን ሴቶች ላይ የመከሰት እድሉ ከወንዶች ይልቅ ሁለት እጥፍ ነው፡፡ የፓኒክ ዲስኦርደር መንስኤዎች ብዙ ሲሆኑ በባህሪያቸው የሚጨነቁ እና ጭንቀት ጎጂ ነው ብለው በሚያስቡ ሰዎች ላይ ይጨምራል፡፡ በተጨማሪም የህይወት ጫና፣ ከሚወዱት ሰው አለመግባባት ወይም መለየት ሊቀሰቅሱት ይችላሉ፡፡ ፓኒክ ዲስኦርደር ያለባቸው ብዙዎቹ ሰዎች ቡና ሲጠጡ የመጨናነቅ ስሜት ይሰማቸዋል፡፡   የፓኒክ ምልክቶች አካላዊ ስለሆኑ ታካሚዎች ወደ የውስጥ ደዌ ወይም የልብ ስፔሻሊስት ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ በምርመራ ግን የሚገኝ ነገር አይኖርም፡፡ ፓኒክ ዲስኦርደር ውጤታማ በሆነ ሁኔታ በንግግር ህክምና ወይም በመድሀኒት ሊታከም ይችላል፡፡ መልካም ጊዜ!

የስብእና ጭንብል

ጭንብል ብዙ አይነት ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዶቹ ግልፅ እና አካላዊ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ግልፅ ያልሆኑ የስብእና ናቸው፡፡ ሁሉም ጭንብሎች ሁለት መሰረታዊ አገልግሎት አላቸው፡፡ ማሳየት የማንፈልገውን መሸፈን እና ማሳየት የምንፈልገውን ማጉላት፡፡ የአእምሮ ህክምና ከስብእና ጭንብል ጋር የሚዋሰንበት ድንበር ሰፊ ነው፡፡ ጥቂት ምሳሌዎች፦ ሀርቬይ ክሊክለይ ሳይኮፓቶችን ሲገልፅ "እነዚህ የ ጤነኛ/ደህና ሰው የሚያስመስል ጭንብል የለበሱ ከጭንብሉ ስር ግን አዎንታዊ ስሜቶች (ፍቅር፣ ርህራሄ፣ ደግነት..) የሌላቸው በተቃራኒው አሉታዊ ስሜቶች (ምቀኝነት፣ ብስጭት፣ ቂም...) የሚተራመሱባቸው ናቸው፡፡" ብሏል፡፡   ካርል ዩንግ ሁላችንም ወክለን የምንጫወተው ምስለ'ኔ እንዳለን ይተነትናል፡፡ ሁላችንም መሆን በምንመኘው እና በእውነታው መካከል ያለውን ልዩነት በምስለ'ኔ ለመሙላት እንሞክራለን፡፡   በሁሉም ቦታ፣ በሁሉም ሁኔታ እውነት ሁሉም ሰው የሚፈልገው ነገር አይደለም፡፡ ለምሳሌ "ስብሰባው ለይስሙላ ነው እንጂ ለውጥ እንዲመጣ ታስቦ የተዘጋጀ አይደለም፡፡" ለማለት አስቸጋሪ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ ወይም አማቻችንን "በዚህ እድሜዎ ሂውማን ሄር ከሚያደርጉ የተፈጥሮ ፀጉርዎ የተሻለ ይመስለኛል፡፡" አንልም፡፡ በማንኛውም ሁኔታ ውሸት ጉንጫችንን ከምትስመን እውነት በጥፊ ብታጮለን የምንመርጥ ስንቶቻችን እንደሆንን እኔ'ነጃ፡፡   አልፎአልፎ በሁኔታዎች አስገዳጅነት ከሆነ ማህበራዊ ትስስር እንዳይላላ ይረዳል፡፡ጭንብል ከተደጋገመ ግን እውነት ይመስልና እውነተኛውን እና ጥልቅ ማንነታችንን እየተውን ጭንብሉን እየመሰልን እንመጣለን፡፡   ፌስ ቡክ ላይ ...

ለሱስ የሚሰጥ የቡድን የንግግር ህክምና

ሰዎች ሱስ እንዲያቆሙ መፍትሄው ምክር የሚመስላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ቁጭ አድርጎ ጉዳቱን ዘርዝሮ ማስረዳት፡፡ የዚህን ዘዴ ውጤታማነት ለመገምገም ስንት ሰው ተመክሮ አቁሟል? የሚለውን መመለስ ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች በአብዛኛው የሚያሳምነን ሌሎች የሚነግሩን ሳይሆን ራሳችን የደረስንበትን ነው፡፡ በሱስ ውስጥ ተከታታይ የሆነ 'ልተው አልተው' የሚል ትግል አለ፡፡ ለሱስ የሚሰጠው የንግግር ህክምና ሰዎች የሚያልፉበትን ትግል ያለ ወቀሳ በመረዳት ለማቆም የሚፈልጉበትን ምክኒያት እና ለማቆም የሚያስችላቸውን መንገድ ራሳቸው እንዲያመነጩ እንዲሁም በራሳቸው ላይ ያላቸው መተማመን እና ተነሳሽነታቸው እንዲጨምር ማገዝ ነው፡፡   የንግግር ህክምናው በግል ወይም በቡድን ሊሰጥ ይችላል፡፡ ለዛሬ በቡድን የሚሰጠውን የንግግር ህክምና እናያለን፡፡ የቡድን የንግግር ህክምና ሶስት አና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች በባለሞያ እየታገዙ የሚደረግ የንግግር ህክምና ሲሆን በቡድን መሆኑ ካሉት ጥቅሞች ጥቂቶቹ፦   ተስፋ፦ በቡድኑ ውስጥ የሚካተቱት ሱስ በማቆም የተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች በመሆናቸው ገና ለማቆም የሚጀምሩ የተለያየ ጊዜ ያቆሙትን ሲመለከቱ ተስፋ ያገኛሉ፡፡   እኔ ብቻ አይደለሁም፦ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሲያገኙ ብቻቸውን እንዳልሆኑ ይረዳሉ፡፡   መረረዳት፦ ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የሚያልፍ ሰው ሁኔታቸውን በተሻለ ስለሚረዳቸው የደህንነት ስሜት ይሰማቸዋል፡፡    በተጨማሪም ከመርህ የመነጨ ሳይሆን ከግል ተሞክሮ የሚያካፍሏቸውን የተለያዩ ዘዴዎች ይማራሉ፡፡   ነፃ መሆን፦ ከሱስ ተያይዞ ብዙ ፍረጃዎች ስላሉ ሰዎች በግልፅ ለመናገር አይደፍሩም፡፡ በቡ...

ሳይኮፓቶች-ህሊና የሌላቸው ሰዎች

ብዙ ሰው ህሊና የሌላቸው ሰዎች አሉ ብሎ ለመቀበል ያስቸግረዋል፡፡ በየጊዜያቱ የሚያደርሱት ሰቅጣጭ ድርጊት ግን ችላ እንዳይባሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ነገር ግን ህሊና የሌላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ስማቸውም ሳይኮፓት ይባላል፡፡ አደገኛ ስእብና ያላቸው ሰዎች ተብሎ ሊተረጎም ይቻላል፡፡   ሳይኮፓቶች ከምንም ነገር በላይ ስልጣንን ያስበልጣሉ፡፡ ከማህበረሰብም ሆነ ከግለሰብ ደህንነት በላይ፡፡ በተጨማሪም ለድርጊቶቻቸው ሀላፊነት አይወስዱም፡፡ የፀፀት ስሜትም አይሰማቸውም፡፡ ሌላኛው አደገኛ የሚያደርጋቸው 'ጭር ሲል' አይወዱም፡፡ ጭንቀት አያውቃቸውም፡፡ ግርግር እና ትርምስ ይወዳሉም ይፈጥራሉም፡፡ ሌሎች ሰዎች ሲጨነቁ ሲተራመሱ እነሱ ሴራ ያጠነጥናሉ፡፡   ለሳይኮፓቶች ሰዎች ሁሉ በሁለት የተከፈሉ ናቸው፡፡ ጠላት እና መጠቀሚያ፡፡ ለመጠቀሚያ ቢሆንላቸው ብቃትም ታማኝነትም ያላቸውን ሰዎች ይመርጣሉ፡፡ ካልሆነ ግን ብቃት ባይኖረውም ታማኝ የሆኑ ሰዎችን ያቀርባሉ፡፡ ያለ ብቃታቸው ቦታ የተሰጣቸው ሰዎች ታማኝነታቸው እንደሚጨምር ስለሚያውቁ፡፡   የማገናዘብ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሳይኮፓቶች በብዛት የሚገኙት እስር ቤት ሲሆን የማገናዘብ አቅማቸው ከፍ ያሉት ግን በሀይማኖት፣ በፖለቲካ እና በንግድ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ይደርሳሉ፡፡   ዶ/ር ሮበርት ሄር በአንድ ሳይኮፓት በደረሰባቸው ተደጋጋሚ ግፍ ምክኒያት ነው ስለ ሳይኮፓት ማጥናት የጀመሩት፡፡ "ሁኔታ አስገድዶት ነው እንጂ ሰው እንደዚህ ክፉ ሊሆን አይችልም!" ቢሉም ያለ ምንም ምክኒያት ጭምር ጉዳት ያደርስባቸዋል፡፡ ከዛ በኃላ ስለ ሳይኮፓቶች ብዙ ጥናት እና ምርምር ያደረጉ ሲሆን "ህሊና የሌላቸው" እና "ሱፍ የለበሱ እባቦች" የሚሉት መ...

የአስተሳሰብ መዛባ

  የአስተሳሰብ መዛባት ምክኒያታዊ ያልሆኑ፣ የተጋነኑ ወይም ከእውነታው ጋር የማይገናኙ ሀሳቦች የሚፈጥር ሲሆን ወደ አሉታዊ ስሜት አና ያልተገባ ፀባይ ያመራሉ፡፡ አስተሳሰብ፣ ስሜት አና ፀባይ ያላቸው ትስስር የ አስተሳሰብ መግራት ህክምና መሰረት ነው፡፡ ብዙ አይነት የአስተሳሰብ መዛባት አይነቶች ቢኖሩም የዛሬው ስለጥቁርና ነጭ አስተሳሰብ ነው፡፡ በጥቁር እና ነጭ አስተሳሰብ ነገሮችን፣ ሁኔታዎችንና ሰዎችን ሁለት ቦታ ከፍሎ በማየት በእያንዳንዱ ገጠመኝ ከማሰብና ከመገምገም ለመገላገል የሚደረግ (ውጤታማ ያልሆነ) ጥረት ሲሆን ምክኒያታዊ ስላልሆነ ስህተት እና አሉታዊ ስሜት ሊፈጥር ይችላል፡፡ የጥቁር እና ነጭ ምሳሌዎች፦    • ስኬት ወይም ውድቀት • ወዳጅ ወይም ጠላት • ክንፍ ያለው መልአክ ወይም ቀንድ ያለው ሴጣን • በጣም ጥሩ ወይም በጣም መጥፎ • ሁልጊዜ ወይም በጭራሽ • እኛ ወይም እነሱ   ነገሮችን በጥቁር እና ነጭ መመደብ በተለይ ያልተለመዱ እና ጫና የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ውስጥ የሀሰት እርግጠኝነት ይሰጣል፡፡ ህይወት ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ ጽንፍ እና ፅነፍ ላይ የሚገኝ ሳይሆን የተለያዩ መጠን ያላቸው ነገርች ህብር ነው፡፡ ራሳችንን በጥቁር እና ነጭ ስናስብ ካገኘነው የሚከተሉት ጥያቄዎችን መጠየቅ ሚዛናዊ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ያግዛሉ፡፡    "ሌላ ምክኒያት ይኖረው ይሆን?" "ሶስተኛ አማራጭ አለ?" " ከድምዳሜዬ የሚቃረን ምሳሌ አለ?"...ወዘተ ስለሌሎቹ የአስተሳሰብ መዛባቶች በሌላ ጊዜ ይቀርባል፡፡ መልካም ጊዜ!

አርት ቴራፒ - በስነ ጥበብ ስነ ልቦናን ማከም

  ፍቅር ይዞት ግጥም ጽፎ የሚያውቅ፣ ለናፍቆቱ ሙዚቃ ያዳመጠ ወይም ናፍቆቱን ሙዚቃ የቀሰቀሰበት የስነ ጥበብን የማከም አቅም የሚረዳው ነው፡፡ አርት ቴራፒ ስነ ጥበብን በመጠቀም ስነ ልቦናን ማከም ነው፡፡   አንዳንድ ስሜቶች በቃላት ለመግለፅ ያስቸግራሉ፡፡ በብሩሽና በቀለም ሲሆን መግለፅ የሚቀላቸው ሰዎች አሉ፡፡ የአእምሮ ህመም ያለባቸው ሰዎች በስነ ጥበብ ራሳቸውን ሲገልፁ የሚጋጩባቸውን ሀሳቦች እና ስሜቶች በተሻለ ሁኔታ ስለሚረዱ ስለራሳቸው ያላቸው ግንዛቤ ከፍ ይላል፡፡   የአርት ቴራፒ ተጨማሪ ጥቅሞች በራስ መተማመን ከፍ ማድረግ፣ የጭንቀትና የመከፋት ስሜትን መቀነስ፣ ያጋጠመን ነገር በተረጋጋ ሁኔታ ማጤን ..ወዘተ ናቸው፡፡ አንዳንድ ታካሚዎች አስደናቂ ስራዎችን ይሰራሉ፡፡ ነገር ግን አርት ቴራፒ ላይ ለመሳተፍ የሚያስፈልገው ችሎታ ሳይሆን ፍላጎት ብቻ ነው፡፡   ከላይ የተመለከተው በአማኑኤል ሆስፒታል አርት ቴራፒ ክፍል በታካሚ የተሰራ ነው፡፡ መልካም ጊዜ!