Skip to main content

Posts

Featured Post

አስፐርገር ሲንድረም (Asperger syndrome)

The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር  ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
Recent posts

ስለማሰብ ማሰብ

ዘመናዊነት፣ ትምህርት፣ፍትህ ከአዲስ የማሰቢያ መንገድ ውጭ ምንድናቸው? የሰው ልጆች እጅግ አስደናቂ ችሎታችን ማሰብ ከመቻላችን በላይ ስለማሰብ ማሰብ መቻላችን ነው፡፡ ስለማሰብ ማሰብ የምናስብበትን መንገድ ለማሻሻል ከማስቻሉም በላይ ሌሎች ሰዎችን በተሻለ ለመረዳት ያስችላል፡፡ ስለምናስበበት መንገድ አብዝተን ባሰብንና ስለሀሳቦቻችን የተረዳነውን ተግባር ላይ ስናውል የበለጠ ደስተኛ የበለጠ ውጤታማ እንሆናለን፡፡   ሀሳባችን እውነታውን ሊወክልም ላይወክልም ይችላል፡፡ "እኔ ያሰብኩት ነው እውነታው!" ብሎ ክችች ማለት ስለማሰብ እያሰብን እንዳልሆነ ያሳያል፡፡ በእንግሊዘኛው Psychic equivalence ይባላል፡፡ምናባችንን ወደ እውነታው ከማምጣት እውነታውን ወደ ምናባችን ለማምጣት እንደመጎተት ነው፡፡ ሀሳባችን ማለት ሙሉ ለሙሉ እኛን አይወክልም፡፡ ሀሳባችን የኛ እንጂ እኛ አይደለም፡፡ ስለማሰብ ማሰብ የአስተሳሰብ ስህተቶቻችንን መለየት፣ ጠቃሚ የሆኑትን ማጠናከር እና ሂደቱን በተከታታይ ማስተዋል ነው፡፡ የንግግር ህክምና(Psychotherapy) በቀላሉ ሲገለፅ ሰዎች ከሀሳባቸው ትንሽ ወደ ወደ ኃላ ብለው ሀሳባቸውን በራሳቸው መመርመርና መለወጥ እንዲችሉ ማገዝ ነው እንጂ ብዙዎች እንደሚመስላቸው ሰዎችን መምከር አይደለም፡፡   አስተሳሰባችንን ስንለውጥ የየራሳችን ትንሿን አለማችንን መለወጥ እንችላለን፡፡   መልካም ጊዜ!

ሁለት ውብ ታሪኮች ከአማኑኤል ሆስፒታል

አማኑኤል ሆስፒታል የሰው ድክመት፣ ውድቀት፣ ህመም ብቻ የሚሰማበት የሚመስላቸው ሰዎች አይጠፉም፡፡ ነገር ግን በየቀኑ የመነሳት፣ የጥንካሬ፣የፅናትና የፍቅር ውብ ታሪኮች ይስተናገዳሉ፡፡ ሁለቱ በዚህ ሳምንት ከገጠመኝ እነሆ፦   1) አማኑኤል የሴቶች ዋርድ የሀኪሞች ክፍል ተቀምጬ ካርድ ላይ እየፃፍኩ ነው፡፡ በሩ ገርበብ ብሏል፡፡ አንድ ታካሚ ከአልጋዋ ከነጋ አልተነሳችም፡፡ የደበራት ትመስላለች፡፡ ገርበብ ባለው በር ትታየኛለች፡፡ አንድ ወጣት ሴት ፍራፍሬ በፌስታል ይዛ ልትጠይቃት ትገባለች። አይኗ ብርት ብሎ ከአልጋዋ ወዲያው ተነሳች። ተቃቀፉ፡፡ በቀናት ውስጥ ያላየንባት ደስታ ውስጥ ሆና መጫወት ጀመሩ፡፡ ጠያቂዎን አውቃታለሁ፡፡ ከሳምንት በፊት እዚሁ ሆስፒታል እዚሁ ክፍል ተኝታ ነበር፡፡ ጓደኛዋን ልትጠይቅ መምጣቷ ነው፡፡ ተኝታ የምትታከመው ድንገት አቀረቀረች፡፡ አይኗን ሳታነሳ ጓደኛዋን "ግን የምንድን ይመስልሻል?" ብላ ጠየቀቻት፡፡ ጓደኛዋ እቅፍ አደረገቻት "እሱ የፈጣሪ ስራ ነው፡፡ እኛ ግን መድሀኒታችንን እንወስዳለን አለቻት፡፡"... አንድ የኩላሊት ጠጠር ቀዶጥገና ሀኪም "ሀኪሙ ጠጠሩን ያወጣል፤ የሚያድነው ግን አምላክ ነው፡፡" ያለው ትውስ አለኝ፡፡   2) ታካሚ ወንድሙን ይዞ ኦፒዲ ይገባል፡፡ መልካቸው በጣም ይለያያል፡፡ "እባካችሁ ተኝቶ ይታከም?" አለን፡፡ "ያልተለመደ ፀባይ ሲታይበት አከራዮቻችን ቤት እንድንለቅ ጠየቁን፡፡ ለትንሽ ጊዜ ቢተኛ?" አለን፡፡ "ቤተሰቦቻችሁ የት ናቸው?" ብዬ ጠየቅኩት፡፡ መልሱ ያልጠበቅኩት ነበር፡፡ "ከተለያየ ቤተሰብ ነው የመጣነው ግን ወንድሜ ነው፡፡ በማደጎ አብረን ነው ያደግ...

ማዶና ፑታና ኮምፕሌክስ

ማዶና ፑታና ኮምሌክስ ሁኔታዊ (Situaional) ስንፈተ ወሲብ ነው፡፡ ከሚወዷት ፍቅረኛ ወይም ሚስት ጋር ሴክስ ለማድረግ አለመቻልና በተቃራኒው ከሴተኛ አዳሪ ጋር ምንም ስንፈት አለመኖር ሲሆን በተለይ ሚስቶች ልጅ ከወለዱ በኀላ የሚፈጠር ነው፡፡ ይህ ስነ ልቦናዊ ኮምፕሌክስ ያለባቸው ሰዎች የፍቅር ስሜት ላላቸው ሰው የሴክስ ፍላጎት አይኖራቸውም፡፡ የሴክስ ፍላጎት ላላቸው ሰው ደግሞ የፍቅር ስሜት የላቸውም፡፡ሴክስና ፍቅር ሳይዋሀዱ እንደ ዘይት እና ውሀ ሆነው አእምሮ ውስጥ ሲቀመጡ የሚፈጠር ነው።   እነዚህ ሰዎች ሴቶችን ሁሉ በሁለት ይከፍላሉ፡፡ ንፅህት እና ባለጌ፡፡ የሚሰማቸውም ፍቅር በሁለት የተከፈለ ነው፡፡ ንፁህ ፍቅርና የብልግና፡፡ ሚስቶቻቸው ልጅ ከወለዱ በኃላ እንደ ሚስት ሳይሆን እንደ እናት ማየት ይጀምራሉ፡፡ ሴክስ ፎሮይድ እንደሚለው ሁሉንም ፀባይ የሚወስን አይሁን እንጂ ከአካላዊ ድርጊቱ ግን የዘለለ ስነ ልቦናዊ እና መንፈሳዊ ትርጉም ያለው እንደሆነ እርግጥ ነው፡፡ ሴክስ 'ባለጌ ነገር' እየተባለ በሚነገርበት ሁኔታ ውስጥ ማደግ የሚያስከትለው ተፅዕኖ ምን ይሆን? ሴክስ አብዛኛው ነገሩ የሚካሄደው በእግሮች መሀል ሳይሆን በጆሮዎች መሀል ነው፡፡ መልካም ጊዜ!

ማስቲሽ ማሽተት፤ቤንዚን መሳብ

ማስቲሽ ወይም ቤንዚን ከሌሎቹ ሱስ አምጪ ነገሮች በተለየ በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉ፣ ውድ ያልሆኑና ህገ ወጥ ያልሆኑ ናቸው። እነዚህ ሶስት ምክኒያቶች እድሜያቸው ለጋ በሆኑና ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ በሚገኙ ልጆች እንዲዘወተሩ አድርጓቸዋል። ለዚህ ድርጊት የሚውሉት የተለያዩ ነዳጆች፣ ማስቲሽ፣ የሚነፉ ቀለሞች ፣ ጥፍር ቀለም ማስለቀቂያዎች እና የተለያዩ የቀለም ማቅጠኛዎች...ወዘተ ናቸው፡፡ የሚሳቡት ኬሚካሎች አንዳንዶች ላይ 'ለቀቅ' የማለት እና የነውጠኝነት ስሜት፣ ሌሎች ላይ ድክምክም ማለት ይፍጠሩ እንጂ በተደጋጋሚ እንዲወሰዱ የሚያደርጋቸው ለተወሰነ ጊዜ የሚቆየው 'የመንሳፈፍ አይነት ደስታ' ነው። ከፍ ባለ መጠን ከተወሰደ የፍርሀት ስሜት፣ የሌሉ ድምጾች መስማት እንዲሁም ለረጅም ጊዜ ሲወሰድ የአእምሮ እድገትና በተለይ የማስታወስ ችሎታ ላይ ጉዳት ያደርሳል፡፡ በሌሎች ሀገራት የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ይህ ችግር በታዳጊዎች ላይ በይበልጥ እንደሚታይና ለመከላከል የሚረዱ ስርአቶች እንዳሏቸው ነው፡፡ በሀገራችን የተሰራ ጥናት አላገኘሁም፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩ ስለመኖሩ ቁጥሮች ባይገኙም የአዲስአበባ ዋና ዋና ጎዳናዎች ግን ይመሰክራሉ፡፡ ትኩረት እንደሚፈልግ አያጠያይቅም! መልካም ጊዜ!

ፈገግተኛ ዲፕረሽን (Smiling depression)

ፈገግተኛ ዲፕረሽን ከተለመደው ዲፕረሽን ወጣ ያለ ሲሆን እነዚህ ሰዎች የሚሰማቸውን መከፋት፣ ተስፋ ማጣት...ወዘተ በውስጣቸው ይዘው በአብዛኛው ፈገግታ የሚታይባቸውና በሌሎች ሰዎች እንደ ደስተኛ የሚታዩ ናቸው፡፡ በአብዛኛው ትዳር/የፍቅር ጓደኛ፣ ስራ አላቸው፡፡ በስራቸው ስኬታማ፣ በማህበራዊ ኑሯቸው ጥሩ ይሁኑ እንጂ ለብቻቸው ሲሆኑ ተስፋ መቁረጥ፣ መሰላቸት፣ የእንቅልፍ ችግር ያጋጥማቸዋል፡፡   ዲፕረሽን ሁሉም ሰው ላይ በተመሳሳይ የሚገለፅ ህመም አይደለም፡፡ ስራውን እየሰራ ስለሆነ ግለሰቡ ራሱ ዲፕረሽን እንዳለበት ላይረዳ ይችላል፡፡ፈገግተኛ ዲፕረሽን ከዲፕረሽን የባሰ የሚያደርገው ዲፕረሽን ያላቸው ሰዎች ራስን የማጥፋት ሀሳብ ቢኖራቸውም ለመሞከር አቅም ስለማይኖራቸው ራስን የማጥፋት እድላቸው(በንፅፅር)ዝቅ ያለ ነው፡፡ በእምነት ጠንካራ መሆንና የልጆች መኖር ራስን ከማጥፋት በከፍተኛ ደረጃ የሚከላከሉ ይሁኑ እንጂ መቶ ከመቶ ያስቀሩታል ማለት አይደለም፡፡   አንዳንድ ፈገግተኛ ዲፕረሽን ያለባቸው ሰዎች ዲፕረሽንን እንደ ድክመት ስለሚያዩት ሞያዊ እርዳታ ለማግኘት ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡ በአጠቃላይ መከፋትን በተመለከተ በጣም አስፈላጊ ነገር ስሜትን መናገር መቻል ነው፦ለጓደኛ፣ ለቤተሰብ እንዲሁም ሞያዊ እገዛ የሚያስፈልግ ከሆነ ከስነ ልቦና ባለሞያ ወይም ከአእምሮ ሀኪም ጋር መነጋገር ጥሩ ነው።   ፈገግተኛ ዲፕረሽን ላይ በብዛት ከሚከሰቱ ስሜቶች አንዱ ብቸኝነት ሲሆን ብቻዎን እንዳልሆኑና ዲፕረሽን ውጤታማ በሆነ መልኩ ሊታከም የሚችል ህመም መሆኑን ማስታወስ ጥሩ ነው፡፡ መልካም ጊዜ!

የእርጅና ስነ ልቦና

እርጅና ሲመጣ የሰዎች ትኩረት ከገንዘብ ወደ ጤንነት ይዛወራል፡፡ በጉልምስና ወቅት ብዙ ሰዎችን የሚያሳስባቸው ከሰው ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት እና ስራ ሲሆን በእርጅና እድሜ የሚከሰተውን አካላዊ ለውጦች ወይም ህመሞችን ተከትሎ የሚያሳስባቸው በይበልጥ አካላዊ ሁኔታ ነው፡፡    በእርጅና እድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ሰባት ተጨማሪ አመታት የሚኖሩ ሲሆን አንድ አያት ብቻ ካለን ብዙ ጊዜ ሴት አያት ነው የሚኖረን።   በእርጅና እድሜ የሚጠበቁ ነገሮች፦  ህይወትን ዞር ብሎ መቃኘት ከቁሳዊ ነገሮች ጋር ያለ ቁርኝት መቀነስ የትዳር አጋር/ ጓደኞችን ማጣት የሚፈጥረውን ሀዘን መቋቋም ከጡረታ ጋር የተያያዙ ለውጦችን መቀበል ከልጅ ልጅ ጋር የሚኖር ግንኙነት...ወዘተ  እንደ ኤሪክሰን በእርጅና እድሜ ላይ ሰዎች ያለፉበትን ይቃኙና ባሳለፉት ህይወት ደስተኛ ከሆኑ እርካታና ሰላም ይሰማቸዋል፡፡ በተጨማሪም ሞትን በፀጋ ለመቀበል ዝግጁ ናቸው፡፡ "ሞት ሆይ መውጊያህ የታለ የሚሉ ይመስላል፡፡"በአንፃሩ ህይወት አጭር እንደሆነ፣ በህይወታቸው ትክክለኛ ውሳኔ እንዳልወሰኑና ለማስተካከል ጊዜ እንደሌላቸው የሚያስቡ ከሆነ ውጤቱ መበሳጨት እና ንጭንጭ ይሆናል፡፡   "አርባ አመት ለወጣቶች የእርጅና እድሜ ሲሆን ለሽማግሌዎች ሀምሳ አመት የወጣትነት እድሜ ነው፡፡" ቪክቶር ሁጎ መልካም ጊዜ!