The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
ሰዎች ሱስ እንዲያቆሙ መፍትሄው ምክር የሚመስላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ቁጭ አድርጎ ጉዳቱን ዘርዝሮ ማስረዳት፡፡ የዚህን ዘዴ ውጤታማነት ለመገምገም ስንት ሰው ተመክሮ አቁሟል? የሚለውን መመለስ ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች በአብዛኛው የሚያሳምነን ሌሎች የሚነግሩን ሳይሆን ራሳችን የደረስንበትን ነው፡፡ በሱስ ውስጥ ተከታታይ የሆነ 'ልተው አልተው' የሚል ትግል አለ፡፡ ለሱስ የሚሰጠው የንግግር ህክምና ሰዎች የሚያልፉበትን ትግል ያለ ወቀሳ በመረዳት ለማቆም የሚፈልጉበትን ምክኒያት እና ለማቆም የሚያስችላቸውን መንገድ ራሳቸው እንዲያመነጩ እንዲሁም በራሳቸው ላይ ያላቸው መተማመን እና ተነሳሽነታቸው እንዲጨምር ማገዝ ነው፡፡ የንግግር ህክምናው በግል ወይም በቡድን ሊሰጥ ይችላል፡፡ ለዛሬ በቡድን የሚሰጠውን የንግግር ህክምና እናያለን፡፡ የቡድን የንግግር ህክምና ሶስት አና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች በባለሞያ እየታገዙ የሚደረግ የንግግር ህክምና ሲሆን በቡድን መሆኑ ካሉት ጥቅሞች ጥቂቶቹ፦ ተስፋ፦ በቡድኑ ውስጥ የሚካተቱት ሱስ በማቆም የተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች በመሆናቸው ገና ለማቆም የሚጀምሩ የተለያየ ጊዜ ያቆሙትን ሲመለከቱ ተስፋ ያገኛሉ፡፡ እኔ ብቻ አይደለሁም፦ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሲያገኙ ብቻቸውን እንዳልሆኑ ይረዳሉ፡፡ መረረዳት፦ ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የሚያልፍ ሰው ሁኔታቸውን በተሻለ ስለሚረዳቸው የደህንነት ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ በተጨማሪም ከመርህ የመነጨ ሳይሆን ከግል ተሞክሮ የሚያካፍሏቸውን የተለያዩ ዘዴዎች ይማራሉ፡፡ ነፃ መሆን፦ ከሱስ ተያይዞ ብዙ ፍረጃዎች ስላሉ ሰዎች በግልፅ ለመናገር አይደፍሩም፡፡ በቡ...