The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
ፈተና ብዙ ጊዜ ብናልፍበትም እንደአዲስ ከሚያስጨንቁን ነገሮች አንዱ ነው፡፡ የፈተና ሰሞን የሚፈጠር ጭንቀት የሚገኘው ውጤት ላይ ተፅእኖ ይኖረዋል፡፡ በመጠኑ ከሆነ ትኩረት ለማድረግ እና ጠንክሮ ለመስራት ሲያግዝ ከበዛ ግን ከቁጥጥር ውጭ ይሆንና ወሳኝ የክለሳ ጊዜ በከንቱ ያልፋል፡፡
የበዛ ጭንቀት ሲኖር የእንቅልፍ መዛባት፣ የሀሳብ መበታተን፣ ድካም ስለሚያስከትል ውጤታማ ጥናት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ከታዩ ጭንቀቱ የበዛ ስለሆነ ለመቆጣጠር መሞከር ያስፈልጋል፡፡ የፈተና ጫናን ለመቋቋም የሚረዱ ነጥቦች እነሆ፦
1. ተስማሚ ጊዜና ቦታ መምረጥ፦
እያንዳንዱ ሰው ለጥናት የሚመርጠው ጊዜና ቦታ አለው፡፡ ጠዋት ጠዋት የሚመቸው አለ፤ ከሰአት እና ምሽት የሚመርጥ አለ፤ ላይብረሪ የሚመረጥ አለ፤ ቤት የሚመርጥ አለ፡፡ በእውነታው ቀኑን ሙሉ ማጥናት አይቻልም፡፡ በተስማሚው ጊዜ በሚፈልጉት ቦታ ማጥናት የተሻለ መረጋጋትን ይፈጥራል፡፡
2. አብረው የማያጠኑ ከሆነ ስለ ትምህርቱ አለመነጋገር፦
ስለፈተና ጭንቀት አና ሌሎች መረጃዎችን መለዋወጥ አስፈላጊ ነው፡፡ አብረው የማያጠኑ ከሆነ ማን ምን እንዳጠና ማወቁ ምንም ጥቅም የለውም፡፡ 'ያላጠናሁት ብዙ አለ፡፡' የሚል ሀሳብ ስለሚፈጥር ጭንቀቱን ያባብሳል፡፡ የተሻለው መንገድ የራስን እቅድ አውጥቶ ለመተግበር መሞከር ነው፡፡ በተለይ ከሁለት ሰዎች መራቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ''ሁሉንም ነገር በደንብ አጥንቻለሁ፡፡" ከሚልና "ምንም ምንም አላጠናሁም፡፡" ብሎ ጭንቀቱን ከሚያጋባ፡፡
3. በቂ እንቅልፍ ማግኘት፦
በእንቅልፍ የሚያልፈው ጊዜ የሚባክን ሳይሆን አእምሮ ባትሪውን ለነገ ስራ ቻርጅ የሚያደርግበት ነው፡፡ ስንተኛ አእምሮአችን ያስገባነውን መረጃ በመልክ በመልኩ የሚያስቀምጥበት ስለሆነ የጥናቱን ያክል አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይ የፈተና ዋዜማ እንቅልፍ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
4. ካለፈ በኃላ ስለፈተናው አለመወያየት፦
ካለፈ በኃላ መልስ ለማረጋገጥ መሞከር ወይም ስለፈተናው መወያየት ጥቅም የሚኖረው በአንድ ሁኔታ ብቻ ነው- ፈተናውን ካለፈ በኃላ ሄዶ ማስተካከል የሚፈቀድ ከሆነ፡፡ የተሰራውን መለወጥ አይቻል ነገር የሚቀጥሉትን ፈተናዎች ዝግጅት ከማበላሸት ስላለፈው ፈተና አለመነጋገር ይመረጣል፡፡
5. የፈተና ቀን፦
ቁርስ፣ ቁርስ፣ ቁርስ!!!፦
ፈተናው ከሰአት ከሆነ፦ ቁርስ፣ ቁርስ፣ ቁርስ!!! ምሳ፣ ምሳ፣ ምሳ!!!!
መልካም ፈተና
Comments
Post a Comment