Skip to main content

Featured Post

አስፐርገር ሲንድረም (Asperger syndrome)

The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር  ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው

ታካሚዎች የህክምና ውጤቱ ጥሩ እንዳልሆነ ሲነገራቸው የሚያልፉባቸው 5ቱ ሂደቶች

ሰዎች ወደ ህክምና ሲሄዱ ህመማቸው ቀላል ህመም እንደሚሆን፤ የህክምናው ውጤትም መሻል ወይም ፈውስ እንደሚሆን ተስፋ አድርገው ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የምርመራው ወይም የህክምናው ውጤት እንደጠበቁት ላይሆን ይችላል፡፡ እንደዛ ሲሆን የሚያልፉባቸው ሂደቶች፦

1. ድንጋጤና ምንም እንዳልተፈጠረ መሆን፦
ልክ ጥሩ ያልሆነ ውጤት እንደሰሙ አስደንጋጭ ስለሚሆን የመጀመሪያው ደረጃ 'ክው' ማለት ሲሆን አልፎአልፎ የህክምና ውጤቱን እንዳልተፈጠረ በመቁጠር ህክምናውን በማቋረጥ እና ወደ ሌሎች ተቋማት ወይም አማራጭ ህክምናዎች(የባህል ወይም የሀይማኖት) ሊሄዱ ይችላሉ፡፡
2. ንዴት፦
ድንጋጤው ሲያልፍ ንዴት ይተካል፡፡ ብዙ ጊዜ "ለምን?" ብለው ይጠይቃሉ፡፡ በፈጣሪ ላይ፣ በዕድላቸው፣ በቤተሰብ፣ በጓደኛ አንዳንዴ በራሳቸው ሊናደዱ ይችላሉ፡፡ ንዴታቸው የህክምና ባለሞያ ወይም የህክምና ተቋሙ ላይም ሊያነጣጥር ይችላል፡፡ የሚያክማቸው ባለሞያ ንዴቱ በግለሰብ ደረጃ የተሰነዘረ ሳይሆን የሚሰማቸውን ስሜት ሲገልፁ የተፈጠረ እንደሆነ አውቆ በተረጋጋ ሁኔታ ስሜታቸውን ለመረዳት ከሞከረ ከንዴቱ ስር ያሉትን የፍርሀት፣ የሀዘን እና የብቸኝነት ስሜቶች ላይ ማተኮር ይቻላል፡
3. መደራደር፦
ንዴቱ ሲያልፍ ሰዎች ከፈጣሪያቸው እንዲሁም ከሀኪማቸው ጋር ለመደራደር ይሞክራሉ፡፡ ለፈጣሪያቸው ፈውስ የሚያገኙ ከሆነ ከአሁን በኃላ መልካም ስራ እንደሚሰሩ፣ ቤተ እምነት እንደሚሄዱ ቃል ይገባሉ፡፡ አንዳንድ ታካሚዎች ለሀኪማቸው 'ጥሩ ታካሚ' ከሆኑ የተሻለ ህክምና እንደሚያገኙ ያስባሉ፡፡ ታካሚዎች ምንም አይነት ፀባይ ቢያሳዩ መደረግ የሚገባው ሁሉ እንደሚደረግላቸው እንዲሁም 'ጥሩ ታካሚ' የሚባለው የሚሰማውን በግልፅ የሚናገር እንደሆነ ልናስታውሳቸው ያስፈልጋል፡፡
4. መከፋት፦
መከፋት ደረጃ ሲደርስ ከሰው መገለል፣ የእንቅልፍ ችግር፣ ተስፋ መቁረጥ ሊከሰት ይችላል፡፡ የመከፋት ምክኒያቶች በህመሙ ሳቢያ ሊፈጠሩ የሚችሉ ከስራ መስጓጎል፣ ከገንዘብ ችግር፣ ከሰዎች መገለል ወይም ስለ ሞት ማሰብ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡(መከፋቱ የበዛ ከሆነ የአእምሮ ህክምና ሊያስፈልገው ይችላል፡፡
5. መቀበል፦
እዚህ ደረጃ ሲደረስ የተፈጠረው ነገር ማንም ሰው ላይ ሊደርስ የሚችል እንደሆነ ይቀበላሉ፡፡ ይህንን መቀበል ደግሞ የተረጋጋ ስሜት ይፈጥራል፡፡
ከElisabeth Kubler-Ross 'On death and dying' የተተረጎመ

Comments

Popular posts from this blog

አራቱ የልጅ አስተዳደግ አይነቶች (Parenting styles)

ልጆች የሚያድጉበት መንገድ ከፍ ሲሉ ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት፣ የፍቅር ጓደኛ ምርጫ፣ ስኬት፣ በራስ መተማመን ላይ ትልቅ ሚና አለው፡፡ በተጨማሪም ከሴክስ፣ከገንዘብና ከአማች ቀጥሎ ትዳር ውስጥ አለመግባባት የሚፈጥረው የልጆች አስተዳደግ ነው፡፡ እንደ የስነ-ነልቦና ባለሞያዎች ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያሳድጉባቸው መንገዶች በአራት ይከፈላሉ፡፡     አምባገነን (ኮስታራ) ፦ ይህ አይነት የልጅ አስተዳደግ በአለማችን በይበልጥ ደግሞ በሀገራችን ለረጅም ጊዜ የነበረ የማሳደጊያ መንገድ ነው፡፡ ከእናቶች ይልቅ ደግሞ አባቶች ላይ ይስተዋላል፡፡ እነዚህ ወላጆች ልጆቻቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው 'ኮስተር' ብለው ይነግሩና ልጆች 'ወለም ዘለም' ሳይሉ እንዲከተሉ ይጠብቃሉ፡፡ እንደዚህ የሚያድጉ ልጆች በአብዛኛው ስኬታማ ለመሆንና 'ትክክል' የሆኑ ነገሮችን ለማድረግ የሚጣጣሩ ሲሆኑ አዲስ ነገር ለመሞከር ወይም ያልተለመደ ስራ ለመስራት ይከብዳቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ከቤተሰብ ሲርቁ የማያምኑባቸውን ነገሮች ለማድረግ ይገፋፋሉ፡፡   የሚያሞላቅቁ (ሁሉንም የሚፈቀዱ)፦ ይሄ የልጅ አስተዳደግ በቅርብ የተጀመረ ሲሆን በከተማዎች በጣም እየተስፋፋ የመጣ አይነት ነው፡፡ እነዚህ ወላጆች ልጆቻቸው ያለ ገደብ እንደፈለጉ አንዲሆኑ ይፈቀዳሉ፡፡ ልጆቻቸው ያለ ከልካይና ያለ ገደብ እንደልባቸው እንዲሆኑ ከመፍቀድ ውጪ ምን ማድረግ እንዳለባቸው አይነግሯቸውም፡፡ ልጆቻቸው እስከፈለጉ ድረስ ከቤተሰቡ አቅም በላይ ቢሆንም እንኳ ለማሟላት ይጣጣራሉ፡፡እንደዚህ የሚያድጉ ልጆች ከቤት ውጭ እንደፈለጉ መሆን ስለማይችሉ ጭንቀት ይሰማቸዋል፡፡ የተወሰኑት ለምንም ነገር ሀላፊነት የማይሰማቸው ይሆናሉ፡፡   ግድ የለሽ፦ እነዚህ ወላ...

ሴክስ የሌለበት ትዳር

ረጅም ጊዜ ትዳር ውስጥ የቆዩ ሰዎች የሆነ ጊዜ ላይ ለረጅም ጊዜ ያለ ሴክስ ሊቆዩ ይችላሉ፡፡ በፊት በየቀኑ ወይም በሁለት ቀን አንዴ የነበረው ቀስ በቀስ ወደ ሳምንታት ከዚያም ወደ ወራት ሊዘልቅ ይችላል፡፡ በጣም አልፎ አልፎ ወይም ምንም ሳያደርጉ ደስተኛ ሆነው የሚኖሩ የተወሰኑ ባለትዳሮች አሉ፡፡ የሚበልጡት ግን አንዳቸው ወይም ሁለቱም ደስተኛ ሳይሆኑ የሚከሰት ነው፡፡ ከአምስቱ የፍቅር ቋንቋዎች ለአካላዊ ንኪኪ ቦታ የሚሰጡ ሰዎች ለረጅም ጊዜ ሴክስ አለማድረግ የአለመፈለግ ስሜት ይፈጥርባቸዋል፡፡ (ስለ አምስቱ የፍቅር ቋንቋዎች ከዚህ በፊት ቀርቧል፡፡) የሚሰማቸውን ስሜትና ሀሳብ ለመግለፅ ሀፍረት ስለሚሰማቸው ዝም ይላሉ፡፡ ዝምታው ሁለቱም ተጣማሪዎች የየራሳቸውን ግምት እንዲወስዱ ያደርጋቸዋል፡፡ (አንዳንድ ጊዜ አደገኛ የሆኑ ግምቶችን) ይህ ደግሞ ደስተኛ አለመሆን፣ መነጫነጭ፣ እንደ ባልና ሚስት ሳይሆን እንደ ደባል መተያየት የመጨረሻ ደረጃ ሲደርስ ደግሞ ፍቺ ሊያስከትል ይችላል፡ የሴክስ ፍላጎት በጊዜና በሁኔታ ከፍ ዝቅ የሚል ነገር ነው፡፡ ብዙ ነገሮችም ይወስኑታል፦ እርግዝና፣ ልጅ መውለድ፣ የስራ ጫና፣ አካላዊ ጤንነት...ወዘተ፡፡ በግልፅ ፍላጎትን፣ ፍርሀት፣ ስጋትን መነጋገር ጥሩ ነው፡፡ ቢቻል ንግግሩ ከመኝታ ቤት ውጨ በተረጋጋ ሁኔታ ቢደረግ ይመረጣል፡፡( መኝታ ቤት ወይም ከሴክስ በኃላ የሚደረጉ ውይይቶች በስሜት የሚደረጉ ስለሚሆኑ ከመፍትሄ ይልቅ ስሜትን የሚጎዱ መወቃቀሶችን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡) መኝታ ቤት የሚኖረው መግባባት ከመኝታ ቤት ውጭ ያለውን መግባባት እንደሚወስነው ከመኝታ ውጭ ያለው መግባባት የመኝታ ቤቱን መግባባት ይጨምረዋል፡፡ በተቃራኒውም ደግሞ እውነት ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ...

አምስቱ የፍቅር ቋንቋዎች

ሁለት ሰዎች የፈለገ ቢዋደዱ የፍቅር ግንኙነታቸው እንዲዘልቅ ትልቅ ጥረት ይጠይቃል፡፡ በዚህ ጥረት ውስጥ የፍቅር ቋንቋ ጉልህ ድርሻ ይይዛል፡፡ የፍቅር ተጣማሪ የሚጠብቀውንና የሚፈልገውን መረዳት የፍቅር ህይወትን ከማሻሻሉ ጋር ተያይዞ በአጠቃላይ ጥሩ ስሜት፣ ደስታና በስራ ላይ ውጤታማነት ያመጣል፡፡ ሰዎች ፍቅራቸውን የሚገልፁባቸው ወይም የተጣማሪያቸውን ድርጊት የሚረዱባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ፡፡ ጠቅለል ተደርገው በአምስት ሊመደቡ ይችላሉ፡፡ እነሆ፦ የፍቅር ቃላት የፍቅር ቃላት ለሚመርጡ ሰዎች ‹‹እወድሃለሁ›› ወይም ‹‹እወድሻለሁ›› የሚሉት ቃላት ትልቅ ትርጉም አላቸው፡፡ በተጨማሪም ከተጣማሪያቸው ለሚሰነዘር አድናቆት ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ፡፡ቃላት የከበረ ዋጋ አላቸው፡፡ በተቃራኒው አሉታዊ ወይንም ስድብ የሚመስል ቃላት ይጎዳቸዋል፡፡ በቀላሉ ይቅር ለማለት ይቸገራሉ፡፡ ጥሩ ጊዜ   ይህ የፍቅር ቋንቋ ለተጣማሪ ያልተከፋፈለ ትኩረት ስለመስጠት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ከቃላት ይልቅ የተጣማሪያቸውን ጊዜና ያልተከፋፈለ ትኩረት ማግኘት ጥሩ ስሜት ይፈጥርላቸዋል፡፡ በተቃራኒው የተከፋፈለ ትኩረት ፣ቀጠሮ መሰረዝና አለመደመጥ ያስከፋቸዋል፡፡ ስጦታ መቀበል   ለአንዳንድ ሰዎች የመወደድ ስሜት እንዲሰማቸው ስጦታዎች ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ቁሳዊያን ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ከስጦታው ይበልጥ ስጦታን ለመስጠት የተደረገው ሀሳብ በስጦታ ሰጪው ያላቸውን ቦታ ያረጋግጥላቸዋል፡፡ ተግባራዊ እገዛ   ለእነዚህ ሰዎች ድርጊቶች ከቃላት ይበልጥባቸዋል፡፡ ተጣማሪያቸው እየለፉ ያለበትን አስቸጋሪ ጉዞ ተረድተው በተግባር ቢያግዟቸው ይመርጣሉ፡፡ ለእነሱ ተግባራዊ እገዛ የማሰብና የፍቅር መገለጫ ነው፡፡ ይህንን ቋንቋ...

አዎንታዊ ስነ ልቦና (Positive Psychology)

የአእምሮ ህመምን ማከም እንደሚያስፈልገው ሁሉ የአእምሮ ጤናን ማጎልበት፣ የሰዎች ድክመት ላይ ከማተኮር ጥንካሬያቸው ላይ ማተኮር፣ ጥሩ ያልሆኑትን ለማቅናት የሚሞክረውን ያህል ምርጥ የሆኑትን አንዲያድጉ ማገዝ የአዎንታዊ ስነልቦና ትኩረቶች ናቸው፡፡ የሰው ልጆችን ኑሮ በተሟላ እና በተመጣጠነ መልኩ ለመረዳት ይሞክራል፡፡ "ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዴት መፍታት ይችላሉ?" ከሚለው መደበኛው የስነ ልቦና ሀሳብ በተቃራኒው የቆመ አይደለም፡፡ በአንጻሩ የተለመደውን ስነ ልቦና የሚያግዝና አድማሱን የሚያሰፋ ነው፡፡ ሰዎች ከውልደት እስከ ሞት የሚያልፉባቸውን ሂደቶች ያጠናል፡፡ ሰዎች መሆን የሚችሉትን 'ምርጡን እራሳቸውን' እንዲሆኑ እንዲሁም የሚያደርጓቸውን ነገሮች በተሻለ መንገድ ማድረግ እንዲችሉ ያግዛል፡፡ በህይወት ውስጥ ጥሩ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ በዛው ልክ መጥፎ ነገሮችም አሉ፡፡ የአዎንታዊ ስነ ልቦና ዋነኛ እሳቤው 'ጥሩ ህይወት' ውጣ ውረድን ከማለፍና ችግሮችን ከመቋቋም ከፍ ያለ መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ ሰዎች በራሳቸው መንገድ ደስተኛ የሚያደርጋቸውንና በህይወታቸው የሚሰማቸውን እርካታ የሚወስኑ ነገሮችን ሲጠየቁ የሚሰጧቸው ምላሾች በሚያስገርም ሁኔታ ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ከአሜሪካ ሚሊየነሮች እስከ የህንድ ጎዳና ተዳዳሪዎች የሰጧቸው ምላሾች ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ቀጥለው የተዘረዘሩት ዘር ፣ ፆታ፣ የትምህርት ደረጃ ሳይለዩ ከደስታና ከአእምሮ ጤንነት ጋር ከፍተኛ ተያያዥነት አላቸው፡፡   ** የጓደኞች መኖር   ** ትዳር   ** ተጫዋች መሆን   ** አመስጋኝ መሆን   ** ሀይማኖተኛ ሰው መሆን   ** መዝና...

ምቀኝነት

ምቀኝነት አንድ ሰው እንዲኖረው የሚፈልገውን ችሎታ፣ ስኬት፣ ንብረት...ወዘተ ሌላ ሰው ሲኖረው የሚፈጠር ስሜት ሲሆን መሰረታዊ ከሆኑት ስሜቶቾ አንጻር ሲታይ የንዴትና የሀዘን ድብልቅ ነው፡፡ ሌላ ሰው የተሻለ ነገር ሲሰራ ወይም ሲኖረው ሁለት አይነት ስሜት ሊፈጥር ይችላል፡፡ አድናቆት ወይም ምቀኝነት፡፡ አድናቆት የሌላውን መሻል በትህትና መቀበል ሲሆን፤ ምቀኝነት በንዴት ላለመቀበል መሞከር ነው፡፡ ማን ማንን ይመቀኛል? ሰዎች የሚመቀኙት ከእነሱ ጋር ተቀራራቢ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎችን ነው፡፡ ጓደኛ፣ ጎረቤት፣ የስራ ባልደረባ ...ወዘተ፡፡ ጫማህን የሚጠርገው ሊስትሮ አንተ የተሻለ ኑሮ ስራ ስላለህ ምቀኝነት አይሰማውም፡፡ ይልቁንም አጠገቡ ያለ ሌላ ሊስትሮ የተሻለ ገንዘብ ሲያገኝ ነው ምቀኝነት የሚሰማው፡፡ ጎረቤትህ የተሻለ ቤት ስትሰራ ምቀኝነት ይሰማው ይሆናል እንጂ አላሙዲን አዲስ ህንፃ ቢሰራ ምንም ስሜት አይፈጥርበትም፡፡ በአጠቃላይ ምቀኛ ከሩቅ አይመጣም፡፡   ምቀኝነት ወይስ ቅናት? አንዳንድ ሰዎች ሁለቱን ሲያቀያይሩ ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን የተለያዩ ስሜቶች ናቸው፡፡ ቅናት ቦታ የምንሰጠው ነገር እንዳይወሰድብን ስንፈራ የሚፈጠር ስሜት ሲሆን እንዳይወሰድ የምንፈልገውን ነገር ለመጠበቅ ጥረት እንድናደርግ የሚገፋፋ ነው፡፡ በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ሲፈጠር ሰዎች ረጅም (አንዳንድ ጊዜ ከልክ ያለፈ) ርቀት እንዲሄዱ ያደርጋል፡፡ ምቀኝነት የሚፈጠረው አንድ ሰው ቢኖረው የሚመኘውን (ነገር ግን የሌለውን) ሌላ ሰው ሲኖረው የሚፈጠር ሲሆን ልዩነቱን ለማጥበብ ሌላውን ካለበት ለማውረድ ወይም ራስን ከፍ ለማድረግ እንዲጣጣር ይገፋፋል፡፡ "አላውቃትም እንዴ እንዴት እንደነበረች..." "እኔ ገንዘብ ሰጥቼው አይደል ስራ የጀመረ...