The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
የንዴት ጥቅሞች
ዘመናዊነት የፈለገውን ያህል ቢስፋፋ አሁንም ሰዎች ሰዎች ላይ ጥቃት ይሰነዘራሉ፡፡ በነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ንዴት ራስን ለመከላከል ጉልበት ይሰጣል፡፡ ድንጋጤ አቅምን አይሰጥም፡፡ ሀዘን ጥንካሬ አይሰጥም፡፡
ንዴት በእለት ተእለት የሚያጋጥሙንን ኢፍትሃዊ ድርጊቶች ለመከላከል የሆነ ነገር እንድናደርግ ያነሳሳል፡፡ በስራ ቦታዎች፣ በማህበራዊ ህይወታችን ለውጥ እንድናደርግ ያደርጋል፡፡ ንዴትን እንደ አላርም ካየነው በስራችን የምንናደድ ከሆነ ሌላ ስራ እንድንፈልግ የሚያስታውስ ደወል ነው፡፡ በማህበራዊ ህይወታችን ንዴት ከተሰማን መነጋገር ያለብን ነገር እንዳለ ወይም አቀራረባችንን መለወጥ እነዳለብን የሚያስታውስ ነው፡፡ ፓለቲካው ንዴት የሚፈጥርብን ከሆነ አሰራሩን ወይም ፖለቲከኞችን ለመለወጥ የሆነ ነገር ማድረግ እንዳለብን የሚጠቁም ነው፡፡
የንዴት ጉዳቶች
ንዴት መንገዳችንን የዘጋውን ነገር በደንብ መረዳት፤ በተጨማሪም እንዴት ማለፍ እንዳለብን ማሰብ እንዳለብን የሚያስታውስ አላረም ነው፡፡ በንዴት ጊዜ ስሜታዊ ስለምንሆን በትክክል ለማሰብ እንቸገራለን፡፡ በንዴት ላይ ሆነው የሚናገሩ ወይም እርምጃ የሚወስዱ ሰዎች በአብዛኛው ሲያልፍ ይፀፀታሉ፡፡ አካላዊ ጉዳት፣ ጓደኝነት ማብቃት ...ወዘተ በንዴት ሰአት እነዚህን ማድረግ ሌላውን ሰው ለማሳመም ራስን እንደመግረፍ ነው፡፡ ንዴትን አዳፍኖ ማለፍ የተለያዩ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ህመሞች ሊያስከትል ይችላል፡፡ በተለይ ለድብርት፣ ጭንቀት፣ የእንቅልፍ ችግር እና የተለያዩ ሱሶች ሊያጋልጥ ይችላል፡፡
በአጠቃላይ ንዴት ሰዎች ተገቢ ያልሆነን ነገር እንዲገዳደሩ፣ ህይወታቸውን በተሻለ መልኩ እንዲለውጡ የሚያስችል ጠቃሚ ስሜት ሲሆን ከቁጥጥር ውጭ ከወጣ ወይም በአግባቡ ካልተገለፀ ጉዳቶች ይኖሩታል፡፡ ንዴትን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል በቀጣይ ይቀርባል፡፡
ንዴት የሌለበት ሳይሆን ንዴትን የምትጠቀሙበት ጊዜ ይሁንላችሁ፡፡
Comments
Post a Comment