The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
ሶሻል ፎቢያ ያለባቸው ሰዎች ሌሎች ሰዎች ባሉበት ዘና ማለት አይቻሉም፡፡ ሌሎች ሰዎች የእነሱን ንግግር ወይም ድርጊት የሚገመግሙና የሚተቹ ስለሚመስላቸው ይፈራሉ፡፡ስህተት እንዳይሰሩና እንዳይዋረዱ ስለሚፈሩ ዘና ብለው እንደሚፈልጉት ከሰዎች ጋር መጫወት ይከብዳቸዋል ፡፡
አብዛኛው ሰው ካልለመደው ሰው ጋር ሲሆን የአለመመቸት ስሜት ይፈጠርበታል፡፡ ሶሻል ፍቢያ ሲሆን ግን ፍርሀቱ በጣም የበዛ ይሆናል፡፡ ሶሻል ፎቢያ ያለባቸው ሰዎች አብሯቸው ያሉ ሰዎች ሲጫወቱ ፣ሲስቁ ፣ሲያወሩ እነሱ መሣተፍ ስለማይችሉ ብቸኝነት ይሰማቸዋል፡፡
ብቻቸውን ግን አይደሉም፡፡ ከአስር ሰው አንዱ ተመሣሣይ ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡ ነገ መንገድ ላይ ሲሄዱ አስር ሰዎች ይቁጠሩ ከዛ ውስጥ አንዱ ሶሻል ፍቢያ አለበት/አለባት፡፡
የሶሻል ፎቢያ ምልክቶች በጥቅቱ፦
-ከቤት ውጪ ምግብ ባይበሉ ይመርጣሉ፡፡ለብቻቸው ሬስቶራንት ገብተው፣ ባዶ ጠረጴዛ ፈልገው፣ 'ያ ሁሉ ሰው' እያያቸው መመገብ ይከብዳቸዋል፡፡
- ዝግጅቶች ላይ በግድ ነው የሚገኙት (እሱንም ከተገኙ!)-እስከቻሉት ድረስ ምክኒያት ፈጥረው ለመቅረት ይሞክራሉ፡፡
- በአብዛኛው የድካም ስሜት ይሰማቸዋል፡፡
- ሰዎች ሲሰበሰቡ ከመጨነቅ ጋር ተያይዞ ልብ ቶሎ ቶሎ መምታት፣ ትንፋሽ ቁርጥ-ቁርጥ ማለት፣ ማላብ
- ነገሮች እጅግ አስከፊ ሊሆኑ እንደሚችሉ በማሰብ መጨናነቅ ፣እንቅልፍ ማጣት
- የፍቅር ቀጠሮች ላይ (በተለይየመጀመሪያዎቹ ላይ) ምን እንደሚባል አለማወቅ...
ከላይ የተዘረዘሩትን ሶሻል ፎቢያ ያለባቸው ሰዎች ይረዱታል፡፡ ሌሎች ግን ቀለል አድርገው ሊያዩት ይችላሉ፡፡ ሶሻል ፎቢያ ተማሪዎች እውቀት እያላቸው ጥሩ ውጤት እንዳይኖራቸው፤ ሰራተኞች ችሎታ እያላቸው የሚገባቸውን እድገት እንዳያገኙ፣ እንዲሁም ለሚወዱት ሰው ፍቅራቸውን መግለፅ እንዳይችሉ ያደረጋል፡፡
ሶሻል ፎቢያን ማሸነፍ ይቻላል ነገር ግን ትዕግስትና ቁርጥኝነት ይጠይቃል፡፡
በራሳችን ልናደረግ የምንችለው
1. ሀሣብን መገምገም፦ በሶሻል ፎቢያ የሚቸገሩ ሰዎች ጭንቀትን የሚያባብሱ ሀሳቦች አላቸው፡፡
ለምሳሌ ፡- ፡"እንደ ሞኝ መቆጠሬ አይቀርም፡፡" "መናገር ስጀምር ድምፄ ይንቀጠቀጥና ራሴን አዋርዳለሁ፡፡ " "አንደፈራሁ ሰዎች ያውቁብኛል፡፡" እነዚህን ሀሣቦች መገመገምና መሞገት ጭንቀቱን ይቀንሣል፡፡
2. ከሰዎች ጋር ሲሰበሰቡ ሌሎች ላይ ማተኮር፤ በራስ ጭንቀት ከመጠመድና ፍርሃትን ስለመሸፈን ከመጨነቅ ሌሎች ሰዎች የሚያደርጉትና የሚናገሩት ነገር ላይ ማተኮር ጭንቀትን ይቀንሳል ፡፡ ሰዎች በአብዘኛው የሚያስቡት ስለራሳቸው ስለሆነ የሚገምተውን ያህል መፍራታችንም አያውቁም፡፡
3. አተነፋፈስን ማስተካከል - በፍርሃት ጊዜ በአብዛኛው ከላይ-ከላይና ቶሎ-ቶሎ ነው የሚተነፈሰው ፡፡ ይህ ጭንቀትን ያባብሳል ፡፡- በቀስታ በጥልቀት መተንፈስ ረጋ ያለ ስሜትን ይፈጥራል ፡፡
4. አነቃቂ ነገሮች የጭንቀት ስሜትን ስለሚያባብሱ እነሱን መቀነስ፡፡
እነዚህ ተደረገው አሁንም ስሜቱ ካለ የህክምና እርዳታ ያስፈልገዋል፡፡
Comments
Post a Comment