The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው
ታካሚዎች የውስጥ ደዌ ወይም የቀዶ ጥገና ሀኪም ጋር ሲሄዱ ከሞላ ጎደል ምን መጠበቅ እንዳለባቸው ያውቃሉ፡፡ የአእምሮ ሀኪም ጋር ሲኬድ ምንድነው የሚያጋጥመው? ምን እንደሚጠብቁ ስለማያውቁ ለመሄድ ያመነታሉ፡፡ ከአእምሮ ህክምና ጋር ተያይዞ የሚነሱ የተሳሳቱ ግምቶች፦ የአእምሮ ህክምና ራሱን ለማያውቅ ሰው ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች በጓደኞቻቸው፣ በቤተሰብ ወይም በሀኪም የአእምሮ ህክምና እንዲያደርጉ ሲመከሩ ደስተኛ አይሆኑም፡፡ "እኔ ራሴን አውቃለሁ፡፡" ይላሉ፡፡ ከባድ የአእምሮ መረበሽ ያለባቸው ሰዎች ህክምና ያስፈልጋቸዋል፡፡ ነገር ግን የአእምሮ ህክምና ከሚያስፈልጋቸው ሰዎች አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት የስራ ጫና ያለባቸው፣ የልጅ አስተዳደግ የሚያስጨንቃቸው፣ ትዳራቸው/የፍቅር ህይወታቸው የሚያሳስባቸው...ወዘተ ናቸው፡፡ የአእምሮ ሀኪሞች አእምሮ ያነብባሉ፡፡ የአእምሮ ሀኪም አእምሮ የሚያነብ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ፡፡ "ይሀው መጥቻለው አንብቡና መድሀኒት ስጡኝ" አይነት አቋም ይዘዉ የሚመጡ ፡፡ የዚህ አይነት ግምት ምንጩ ባህላዊና ሀይማኖታዊ ህክምናዎች ናቸው፡፡ አእምሮ አናነብም!! ታካሚን ለመረዳትና ለመርዳት የሚሰማውንና የሚያስበውን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ጥያቄዎች ልንጠይቅ እንችላለን ሆኖም ታካሚዎች ምቾት የማይሰጣቸው ከሆነ ያለመመለስ ፍላጎታቸውን እናከብራለን፡፡ በተጨማሪም ራስን ወይም ሌላን ሰው ስለመጉዳት ካልሆነ በቀር የምንነጋገራቸው ነገሮች በሀኪም እና በታካሚ መሀከል የሚጠበቅ ሚስጥር ነው፡፡ የኔን አይነት ነገርማ ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ያጋጠማቸው ሁኔታ ወይም የሚያስቡት ሀሳብ የሚከብድ ነው ብለው ሲገምቱ ተረካቸውን ለማስተካከል ይሞክራሉ፡፡ ...