Skip to main content

Featured Post

አስፐርገር ሲንድረም (Asperger syndrome)

The big bang theory ላይ የተሳለው ገፀ ባህሪ ሼልደን ኩፐር ለአስፐርገር  ሲንድረም ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናቱ ሁለቴ የአእምሮ ሀኪም ጋር ወስዳው ምንም የአእምሮ እክል የለብህም ቢባልም የሚያሳያቸው ፀባዮች አስፐርገር ሲንድረም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ አስፐርገር ሲንድረም ሰዎች አለምን የሚያዩበትን መንገድ እንዲሁም ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙኘት የሚለውጥ ከኦቲዝም ህብር ህመሞች አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች የሌሎች ሰዎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር፣ ለውጥ አለመፈለግ፣ ተመሳሳይ ነገሮችን ደጋግሞ መስራት ይታይባቸዋል፡፡ ከሌሎች የኦቲዝም ህብር ህመሞች በተሻለ የቋንቋ ክህሎታቸው እና አጠቃላይ የመገንዘብ /የመረዳት ችሎታቸው (ማህበራዊ ግንኙነትን ሳይጨምር) ጥሩ ነው፡፡ የተሻለ የመገንዘብና የንግግር ችሎታ ቢኖራቸውም ቋንቋን ሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ በተለይም ሽሙጥ፣ ስላቅን ለመረዳት ይቸገራሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን እንደወረደ በጥሬው ነው የሚረዱት፡፡ አስፐርገር መገለጫው ከሰው ሰው ስለሚለያይ መኖሩን በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ህምናው በዋናነት ቶሎ መለየትና የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ነው፡፡ መልካም ጊዜ! ዶ/ር ዮናስ ላቀው

ምላሴ/ አፌ ላይ አለ

ባለፈው የሄድንበት ቦታ የት ነበር? ...እ .እ ምላሴ ላይ አለ፡፡ ከስሙ በስተቀር ሌሎች ዝርዝሮችን ልናስታውስ እንችላለን፡፡ ይህ በሳምንት አንዴ አብዛኛው ሰው ላይ የሚያጋጥም ነገር ነው፡፡ በስነ ልቦና የሚታወቅ ክስተት ሲሆን ሌቶሎጂካ (lethologica) ይባላል፡፡ እድሜ ሲጨምር እየተደጋገመ ይመጣል፡፡ በጊዜያዊነት አንድን ነገር መርሳታችንን ተከትሎ ለጥቂት ደቂቃዎችም ቢሆን በቃላት ለመግለፅ የሚያስቸግር የጭንቀት ስሜት ይፈጥራል፡፡
"ምላሴ/አፌ ላይ ነው።" ግን ምንድነው? ሌቶሎጃካ አለማቀፋዊና በሁሉም ቋንቋዎች የሚከሰት መረጃን ሸራርፎ ማስታወስ ነው፡፡ ቋንቋ ምንም ያህል የተወሳሰበ ሂደት ቢሆንም አእምሯችን ሀሳቦችን ወደ ቃላት በከፍተኛ ቅልጥፍና ስለሚለውጣቸው እንደስራ አንወስደውም(በብዛት)።ቃሉ ምላሳችን ላይ ሲሆን እንደምናውቀው እናውቃለን፣ የሰማንበት ቦታ ወይም የመጀመሪያዐው ፊደል ትዝ ይለናል፡፡ ግን ቃሉ የለም፡፡ ምክኒያቱ አእምሯችን የአንድን ቃል ድምፀቱን አንድ ቦታ፣ ፊደሉን ሌላ ቦታ፣ የሚወክለውን ሀሳብ ሌላ ቦታ ሴቭ ስለሚያደርግ ነው፡፡በድንገት ይመጣልንንና ወይም ሰው ሲያስታውሰን 'እፎይ' እንላለን፡፡
 
ይህ ክስተት በሳይንሳዊ ስያሜው ሌቶሎጂካ ቢባልም በአማርኛ "ምላሴ/አፌ ላይ ነው፡፡" በትግርኛ "ኣብዛ ኣፈይ እያ ዘላ" በኦሮምኛ "arraba koo irra jira" ይባላል፡፡ በፈረንሳይኛም በኮርያኛም በሁሉም ቋንቋ ተመሳሳይ ምላሴ ወይም አፌ ላይ ነው የሚል ትርጉም ነው ያለው፡፡
 
አስተማሪ፡ H2SO4 የምን ፎርሙላ ነው? ተማሪ፡ ምላሴ ላይ አለ፡፡ አስተማሪ፡ ሰልፈሪክ አሲድ ነው ያቃጥልኸል ትፋው፡፡

መልካም ጊዜ!

Comments

Popular posts from this blog

ስለማሰብ ማሰብ

ዘመናዊነት፣ ትምህርት፣ፍትህ ከአዲስ የማሰቢያ መንገድ ውጭ ምንድናቸው? የሰው ልጆች እጅግ አስደናቂ ችሎታችን ማሰብ ከመቻላችን በላይ ስለማሰብ ማሰብ መቻላችን ነው፡፡ ስለማሰብ ማሰብ የምናስብበትን መንገድ ለማሻሻል ከማስቻሉም በላይ ሌሎች ሰዎችን በተሻለ ለመረዳት ያስችላል፡፡ ስለምናስበበት መንገድ አብዝተን ባሰብንና ስለሀሳቦቻችን የተረዳነውን ተግባር ላይ ስናውል የበለጠ ደስተኛ የበለጠ ውጤታማ እንሆናለን፡፡   ሀሳባችን እውነታውን ሊወክልም ላይወክልም ይችላል፡፡ "እኔ ያሰብኩት ነው እውነታው!" ብሎ ክችች ማለት ስለማሰብ እያሰብን እንዳልሆነ ያሳያል፡፡ በእንግሊዘኛው Psychic equivalence ይባላል፡፡ምናባችንን ወደ እውነታው ከማምጣት እውነታውን ወደ ምናባችን ለማምጣት እንደመጎተት ነው፡፡ ሀሳባችን ማለት ሙሉ ለሙሉ እኛን አይወክልም፡፡ ሀሳባችን የኛ እንጂ እኛ አይደለም፡፡ ስለማሰብ ማሰብ የአስተሳሰብ ስህተቶቻችንን መለየት፣ ጠቃሚ የሆኑትን ማጠናከር እና ሂደቱን በተከታታይ ማስተዋል ነው፡፡ የንግግር ህክምና(Psychotherapy) በቀላሉ ሲገለፅ ሰዎች ከሀሳባቸው ትንሽ ወደ ወደ ኃላ ብለው ሀሳባቸውን በራሳቸው መመርመርና መለወጥ እንዲችሉ ማገዝ ነው እንጂ ብዙዎች እንደሚመስላቸው ሰዎችን መምከር አይደለም፡፡   አስተሳሰባችንን ስንለውጥ የየራሳችን ትንሿን አለማችንን መለወጥ እንችላለን፡፡   መልካም ጊዜ!

አራቱ የልጅ አስተዳደግ አይነቶች (Parenting styles)

ልጆች የሚያድጉበት መንገድ ከፍ ሲሉ ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት፣ የፍቅር ጓደኛ ምርጫ፣ ስኬት፣ በራስ መተማመን ላይ ትልቅ ሚና አለው፡፡ በተጨማሪም ከሴክስ፣ከገንዘብና ከአማች ቀጥሎ ትዳር ውስጥ አለመግባባት የሚፈጥረው የልጆች አስተዳደግ ነው፡፡ እንደ የስነ-ነልቦና ባለሞያዎች ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያሳድጉባቸው መንገዶች በአራት ይከፈላሉ፡፡     አምባገነን (ኮስታራ) ፦ ይህ አይነት የልጅ አስተዳደግ በአለማችን በይበልጥ ደግሞ በሀገራችን ለረጅም ጊዜ የነበረ የማሳደጊያ መንገድ ነው፡፡ ከእናቶች ይልቅ ደግሞ አባቶች ላይ ይስተዋላል፡፡ እነዚህ ወላጆች ልጆቻቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው 'ኮስተር' ብለው ይነግሩና ልጆች 'ወለም ዘለም' ሳይሉ እንዲከተሉ ይጠብቃሉ፡፡ እንደዚህ የሚያድጉ ልጆች በአብዛኛው ስኬታማ ለመሆንና 'ትክክል' የሆኑ ነገሮችን ለማድረግ የሚጣጣሩ ሲሆኑ አዲስ ነገር ለመሞከር ወይም ያልተለመደ ስራ ለመስራት ይከብዳቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ከቤተሰብ ሲርቁ የማያምኑባቸውን ነገሮች ለማድረግ ይገፋፋሉ፡፡   የሚያሞላቅቁ (ሁሉንም የሚፈቀዱ)፦ ይሄ የልጅ አስተዳደግ በቅርብ የተጀመረ ሲሆን በከተማዎች በጣም እየተስፋፋ የመጣ አይነት ነው፡፡ እነዚህ ወላጆች ልጆቻቸው ያለ ገደብ እንደፈለጉ አንዲሆኑ ይፈቀዳሉ፡፡ ልጆቻቸው ያለ ከልካይና ያለ ገደብ እንደልባቸው እንዲሆኑ ከመፍቀድ ውጪ ምን ማድረግ እንዳለባቸው አይነግሯቸውም፡፡ ልጆቻቸው እስከፈለጉ ድረስ ከቤተሰቡ አቅም በላይ ቢሆንም እንኳ ለማሟላት ይጣጣራሉ፡፡እንደዚህ የሚያድጉ ልጆች ከቤት ውጭ እንደፈለጉ መሆን ስለማይችሉ ጭንቀት ይሰማቸዋል፡፡ የተወሰኑት ለምንም ነገር ሀላፊነት የማይሰማቸው ይሆናሉ፡፡   ግድ የለሽ፦ እነዚህ ወላ...

ሁለት ውብ ታሪኮች ከአማኑኤል ሆስፒታል

አማኑኤል ሆስፒታል የሰው ድክመት፣ ውድቀት፣ ህመም ብቻ የሚሰማበት የሚመስላቸው ሰዎች አይጠፉም፡፡ ነገር ግን በየቀኑ የመነሳት፣ የጥንካሬ፣የፅናትና የፍቅር ውብ ታሪኮች ይስተናገዳሉ፡፡ ሁለቱ በዚህ ሳምንት ከገጠመኝ እነሆ፦   1) አማኑኤል የሴቶች ዋርድ የሀኪሞች ክፍል ተቀምጬ ካርድ ላይ እየፃፍኩ ነው፡፡ በሩ ገርበብ ብሏል፡፡ አንድ ታካሚ ከአልጋዋ ከነጋ አልተነሳችም፡፡ የደበራት ትመስላለች፡፡ ገርበብ ባለው በር ትታየኛለች፡፡ አንድ ወጣት ሴት ፍራፍሬ በፌስታል ይዛ ልትጠይቃት ትገባለች። አይኗ ብርት ብሎ ከአልጋዋ ወዲያው ተነሳች። ተቃቀፉ፡፡ በቀናት ውስጥ ያላየንባት ደስታ ውስጥ ሆና መጫወት ጀመሩ፡፡ ጠያቂዎን አውቃታለሁ፡፡ ከሳምንት በፊት እዚሁ ሆስፒታል እዚሁ ክፍል ተኝታ ነበር፡፡ ጓደኛዋን ልትጠይቅ መምጣቷ ነው፡፡ ተኝታ የምትታከመው ድንገት አቀረቀረች፡፡ አይኗን ሳታነሳ ጓደኛዋን "ግን የምንድን ይመስልሻል?" ብላ ጠየቀቻት፡፡ ጓደኛዋ እቅፍ አደረገቻት "እሱ የፈጣሪ ስራ ነው፡፡ እኛ ግን መድሀኒታችንን እንወስዳለን አለቻት፡፡"... አንድ የኩላሊት ጠጠር ቀዶጥገና ሀኪም "ሀኪሙ ጠጠሩን ያወጣል፤ የሚያድነው ግን አምላክ ነው፡፡" ያለው ትውስ አለኝ፡፡   2) ታካሚ ወንድሙን ይዞ ኦፒዲ ይገባል፡፡ መልካቸው በጣም ይለያያል፡፡ "እባካችሁ ተኝቶ ይታከም?" አለን፡፡ "ያልተለመደ ፀባይ ሲታይበት አከራዮቻችን ቤት እንድንለቅ ጠየቁን፡፡ ለትንሽ ጊዜ ቢተኛ?" አለን፡፡ "ቤተሰቦቻችሁ የት ናቸው?" ብዬ ጠየቅኩት፡፡ መልሱ ያልጠበቅኩት ነበር፡፡ "ከተለያየ ቤተሰብ ነው የመጣነው ግን ወንድሜ ነው፡፡ በማደጎ አብረን ነው ያደግ...

አዎንታዊ ስነ ልቦና (Positive Psychology)

የአእምሮ ህመምን ማከም እንደሚያስፈልገው ሁሉ የአእምሮ ጤናን ማጎልበት፣ የሰዎች ድክመት ላይ ከማተኮር ጥንካሬያቸው ላይ ማተኮር፣ ጥሩ ያልሆኑትን ለማቅናት የሚሞክረውን ያህል ምርጥ የሆኑትን አንዲያድጉ ማገዝ የአዎንታዊ ስነልቦና ትኩረቶች ናቸው፡፡ የሰው ልጆችን ኑሮ በተሟላ እና በተመጣጠነ መልኩ ለመረዳት ይሞክራል፡፡ "ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዴት መፍታት ይችላሉ?" ከሚለው መደበኛው የስነ ልቦና ሀሳብ በተቃራኒው የቆመ አይደለም፡፡ በአንጻሩ የተለመደውን ስነ ልቦና የሚያግዝና አድማሱን የሚያሰፋ ነው፡፡ ሰዎች ከውልደት እስከ ሞት የሚያልፉባቸውን ሂደቶች ያጠናል፡፡ ሰዎች መሆን የሚችሉትን 'ምርጡን እራሳቸውን' እንዲሆኑ እንዲሁም የሚያደርጓቸውን ነገሮች በተሻለ መንገድ ማድረግ እንዲችሉ ያግዛል፡፡ በህይወት ውስጥ ጥሩ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ በዛው ልክ መጥፎ ነገሮችም አሉ፡፡ የአዎንታዊ ስነ ልቦና ዋነኛ እሳቤው 'ጥሩ ህይወት' ውጣ ውረድን ከማለፍና ችግሮችን ከመቋቋም ከፍ ያለ መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ ሰዎች በራሳቸው መንገድ ደስተኛ የሚያደርጋቸውንና በህይወታቸው የሚሰማቸውን እርካታ የሚወስኑ ነገሮችን ሲጠየቁ የሚሰጧቸው ምላሾች በሚያስገርም ሁኔታ ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ከአሜሪካ ሚሊየነሮች እስከ የህንድ ጎዳና ተዳዳሪዎች የሰጧቸው ምላሾች ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ቀጥለው የተዘረዘሩት ዘር ፣ ፆታ፣ የትምህርት ደረጃ ሳይለዩ ከደስታና ከአእምሮ ጤንነት ጋር ከፍተኛ ተያያዥነት አላቸው፡፡   ** የጓደኞች መኖር   ** ትዳር   ** ተጫዋች መሆን   ** አመስጋኝ መሆን   ** ሀይማኖተኛ ሰው መሆን   ** መዝና...

ምቀኝነት

ምቀኝነት አንድ ሰው እንዲኖረው የሚፈልገውን ችሎታ፣ ስኬት፣ ንብረት...ወዘተ ሌላ ሰው ሲኖረው የሚፈጠር ስሜት ሲሆን መሰረታዊ ከሆኑት ስሜቶቾ አንጻር ሲታይ የንዴትና የሀዘን ድብልቅ ነው፡፡ ሌላ ሰው የተሻለ ነገር ሲሰራ ወይም ሲኖረው ሁለት አይነት ስሜት ሊፈጥር ይችላል፡፡ አድናቆት ወይም ምቀኝነት፡፡ አድናቆት የሌላውን መሻል በትህትና መቀበል ሲሆን፤ ምቀኝነት በንዴት ላለመቀበል መሞከር ነው፡፡ ማን ማንን ይመቀኛል? ሰዎች የሚመቀኙት ከእነሱ ጋር ተቀራራቢ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎችን ነው፡፡ ጓደኛ፣ ጎረቤት፣ የስራ ባልደረባ ...ወዘተ፡፡ ጫማህን የሚጠርገው ሊስትሮ አንተ የተሻለ ኑሮ ስራ ስላለህ ምቀኝነት አይሰማውም፡፡ ይልቁንም አጠገቡ ያለ ሌላ ሊስትሮ የተሻለ ገንዘብ ሲያገኝ ነው ምቀኝነት የሚሰማው፡፡ ጎረቤትህ የተሻለ ቤት ስትሰራ ምቀኝነት ይሰማው ይሆናል እንጂ አላሙዲን አዲስ ህንፃ ቢሰራ ምንም ስሜት አይፈጥርበትም፡፡ በአጠቃላይ ምቀኛ ከሩቅ አይመጣም፡፡   ምቀኝነት ወይስ ቅናት? አንዳንድ ሰዎች ሁለቱን ሲያቀያይሩ ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን የተለያዩ ስሜቶች ናቸው፡፡ ቅናት ቦታ የምንሰጠው ነገር እንዳይወሰድብን ስንፈራ የሚፈጠር ስሜት ሲሆን እንዳይወሰድ የምንፈልገውን ነገር ለመጠበቅ ጥረት እንድናደርግ የሚገፋፋ ነው፡፡ በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ሲፈጠር ሰዎች ረጅም (አንዳንድ ጊዜ ከልክ ያለፈ) ርቀት እንዲሄዱ ያደርጋል፡፡ ምቀኝነት የሚፈጠረው አንድ ሰው ቢኖረው የሚመኘውን (ነገር ግን የሌለውን) ሌላ ሰው ሲኖረው የሚፈጠር ሲሆን ልዩነቱን ለማጥበብ ሌላውን ካለበት ለማውረድ ወይም ራስን ከፍ ለማድረግ እንዲጣጣር ይገፋፋል፡፡ "አላውቃትም እንዴ እንዴት እንደነበረች..." "እኔ ገንዘብ ሰጥቼው አይደል ስራ የጀመረ...